የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ በፋይናንስ ስራ አመራር ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ሙያተኞች አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ በፋይናንስ ስራ አመራር ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ሙያተኞች አስመረቀ
አዲስ አበባ ፤ህዳር 03 / 2016 (ኢዜአ)፦ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ በፋይናንስ ስራ አመራር ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ሙያተኞች አስመረቀ።
የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ፣ የዕዙን ማሰልጠኛ ጨምሮ በስሩ ካሉ ሁሉም ክፍለጦሮች ለተውጣጡ የሠራዊት አባላት በግዥ፣ በፋይናንስ፣ በንብረትና በጀት የሙያ ዘርፍ በወንዶ ጢቃ ወታደራዊ ሰፈር ያሰለጠናቸውን ሙያተኞች በደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አስመርቋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የዕዙ ፋይናንስ ስራ አመራር ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል መርጋ ቀልቤሳ፣ ሰልጣኞች ከሙያችሁ ባሻገር ውስጣዊ አንድነታችሁን ማጠናከር ይገባችኋል ብለዋል።
ሰልጣኞች በሰለጠኑበት ሙያ በቅንነትና በታማኝነት ተቋማቸውን ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ሰልጣኞች በስልጠና ቆይታቸው በእያንዳንዱ የሙያ ዘርፍ በንድፈ-ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠና መውሰዳቸውንና በፈተና ተመዝነው ብቁ መሆናቸው ተረጋግጦ ለምረቃ መብቃታቸውን የስልጠናው አስተባባሪ ሌተናል ኮሎኔል ገነነው ግዛው በሪፖርታቸው ገልፀዋል።
ሰልጣኞች በበኩላቸው በስራቸው ውጤታማ ሊያደርጋቸው የሚችል ስልጠና መውሰዳቸውን ገልፀው፤ ወደየክፍላቸው ተመልሰው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ስራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
ለሰልጣኞች እና ለአሰልጣኞች የምስክር ወረቀትና በስልጠናው ብልጫ ላመጡት ሽልማት መስጠቱን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።