የአፍሪካ አቬሽን ባለሙያዎች የዘርፉን ትርፋማነት በሚያሳድጉ ሁኔታዎች ዙርያ ሊመክሩ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2016(ኢዜአ)፦የአፍሪካ አቬሽን ባለሙያዎች  የዘርፉን  ትርፋማነት ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙርያ እንደሚመክሩ ተገለጸ።

55ኛው የአፍሪካ አየር መንገዶች ሕብረት አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት በዩጋንዳ ካምፓላ ይካሄዳል።

ከ500 በላይ የዘርፉ ተዋንያን እንደሚሳተፉበት በሚጠበቀው ይህ ጠቅላላ ጉባኤ በአቬሽን ዘርፉ ከፍተኛ የቢዝነስ ትስስርን ለመፍጠር ያለመ ነው ።

የዩጋንዳ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄኔፈር ባሙቱካሪ እንደተናገሩት በጉባኤው ከ30 በላይ አየር መንገዶች የሚሳተፉ ሲሆን አፍሪካ ያላትን እምቅ አቅም ለማሳደግ የሚችሉ ሀሳቦች እንደሚነሱበት ይጠበቃል።

በጉባኤው የአቬሽን ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ምክክርም እንደሚካሄድ ተናግረው የአፍሪካ አየር መንገዶች በዘርፉ ትርፋማነትን ማሳደግ የሚችሉበት ውይይት የጉባኤው ዋና አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።

በአህጉሩ ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር የሚደረግ በረራን በነጻ ቀጣና ማካሄድም የጉባኤው ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አብራርተዋል።

ሴቶች በአቬሽን ዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግም ና የሴቶች አቬሽን  ማህበር ማቋቋምም  ተጨማሪ የጉባኤው አጀንዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአፍሪካ አየር መንገዶች ሕብረት አመታዊ ጉባኤ በዘርፉ ከሚካሄዱ ግዙፍ ጉባኤዎች ግንባር ቀደሙ መሆኑን ደይሊ ሞኒተር ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም