የዘንድሮው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን እኩልነትና የአብሮነት እሴትን በሚያጎለብቱ ሁነቶች  ይከበራል

 አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2016 (ኢዜአ)፦18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማስጠበቅ የእኩልነትና የአብሮነት እሴትን በሚያጎለብቱ ሁነቶች እንደሚከበር  የፌደሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ። 

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የበዓሉን አከባበር አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸውም 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን  "ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ይከበራል ብለዋል። 

በዓሉም  በሁሉም ክልሎች በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር፤  ህዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ የማጠቃለያ ፕሮግራም እንደሚካሄድ ገልጸዋል። 

የዘንድሮው  የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማስጠበቅ የእኩልነትና የአብሮነት እሴትን በሚያጎለብቱ ሁነቶች ለማክበር ዝግጀት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዓሉም በህዳር 25 የወንድማማችነት ቀን፣ ህዳር 26 የብዝሃነት ቀን፣ ህዳር 27 የአብሮነት ቀን፣ ህዳር 28 የመደመር ቀን፣ ህዳር 29 የኢትዮጵያ ቀን በሚል መሪ ሃሳቦች እንደሚከበር አንስተዋል። 

በጅግጅጋ ከተማ በሚኖረው ዝግጅትም የባህላዊ አልባሳት ትዕይንት፣ ስፖርታዊ ውድድር፣ የንግድ ትርዒትና ባዛር፣ የምክክር መድረክና ሲምፖዚም እንደሚካሄደም ነው ያስታወቁት። 

የፌደሬሽን ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን  ሚያዚያ 21ቀን 1998 ዓ.ም በ3ኛ የፓርላማ ዘመን በ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን  በ2ኛ መደበኛ ስብሰባው በየዓመቱ እንዲከበር ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም