ቀጥታ፡

386ኛው የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ሕብረት ሲምፖዚየም ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2016(ኢዜአ)፦ የዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ሕብረት 386ኛ ሲምፖዚየም ዛሬ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።

ሲምፖዚየሙ የሚካሄደው "ጥቁር ሰማይና የስነ-ፈለክ ቅርሶች አስትሮ ቱሪዝምን ለማሳደግ ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

በሲምፖዚየሙ ላይ ከአፍሪካ፣ ከእስያና አውሮፓ ጨምሮ ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የመጡ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

ሲምፖዚየሙ የተዘጋጀው በዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ሕብረት (IAU)፣ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ቱሪዝም ሚኒስቴር የጋራ ትብብር ነው።

የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የቀጣናዊ ትስስር መሪ ስራ አስፈጻሚና የሲምፖዚየሙ ሰብሳቢ አቶ አለምዬ ማሞ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሲምፖዝየሙ  የስነ -ፈለክ ቅርሶች የተመለከቱ ምርምሮች የሚቀርቡበትና የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ነው።

የስነ-ፈለክ ቱሪዝም ለማሳደግና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን እምቅ የጨለማ ሰማይ የቱሪዝም ሀብት ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚካሄድም አመልክተዋል።

ከቱሪዝም ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር በዘርፉ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግና የቱሪዝም ሀብቱን መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።

ሲምፖዚየሙ እስከ ሕዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ሕብረት ሲምፖዚየም ስታዘጋጅ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ በፊት እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2019 356ኛውን የሕብረቱን ሲምፖዚየም ማስተናገዷ የሚታወስ ነው።

እ.አ.አ በ1919 የተቋቋመው ዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ሕብረት ኢትዮጵያን ጨምሮ 85 አባል አገራት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም