የአፍሪኤግዚም ባንክ ለአፍሪካ የፊልም ኢንዱስትሪዎች 1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪኤግዚም ባንክ ለአፍሪካ የፊልም ኢንዱስትሪዎች 1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2016(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ (አፍሪኤግዚም) የአፍሪካ የፊልም ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር መመደቡን ገለጸ።
የባንኩ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ካናዮ አዋኒ በግብጽ በተካሄደ የአፍሪካ የንግድ ጉባኤ እንደተናገሩት የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ በአህጉሪቱን የፊልም ኢንዱስትሪዎችን አቅም ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
እ.አ.አ በ2022 ባንኩ ለአፍሪካ የሙዚቃ፣ ፊልም፣ ስፖርትና ሌሎች ኪነጥበባዊ ዘርፎች 600 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ከወራት በኋላ በሚጀምረው የፈረንጆቹ አዲስ አመትም ለአፍሪካ የፊልም ኢንዱስትሪዎች በስቱዲዮ ግንባታ፣ ፊልም ቀረጻ እንዲሁም ለፊልም ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል አንድ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ለአብነትም በ2024 አየር ላይ ለሚውሉ የደቡብ አፍሪካ፣ ኬኒያና ናይጄሪያ ፊልሞች የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በሴክተሩ የሚታየውን የመሰረተ ልማትና ቴክኖሎጂ፣ የገበያ ተደራሽነት እንዲሁም የብቁ ባለሙያ ችግርን ለመቅረፍ የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ እየሰራ እንደሚገኝ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው መናገራቸውን ናይጄሪያን ትሪቡን ዘግቧል።
የአፍሪካ የፊልም ኢንዱሰትሪ በየአመቱ ከጠቀላላ የሀገር ውስጥ ምርት 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ እድል መፍጠሩን በመረጃው ተመልክቷል።