በህገ-ወጥ መንገድ ከ500 ኪ.ግ በላይ ጫት ከሀገር ሊያስወጡ የነበሩ ስምንት ግለሰቦች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ-ወጥ መንገድ ከ500 ኪ.ግ በላይ ጫት ከሀገር ሊያስወጡ የነበሩ ስምንት ግለሰቦች ተያዙ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 03/2016(ኢዜአ)፦ በህገ-ወጥ መንገድ ከ500 ኪ.ግ በላይ ጫት ከሀገር ሊያስወጡ የነበሩ ስምንት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።
ግለሰቦቹ መነሻቸውን አዲስ አበባ አደርገው በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል ወደ እንግሊዝ ለንደን፣ ሊያዘዋውሩ እንደነበረም ታውቋል።
በ16 ሻንጣዎች ታሽጎ ወደ ውጭ ሊላክ ሲል የተያዘው 509.32 ኪ.ግ እርጥብ ጫት በኤርፖርቱ በተዘረጋው ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር አማካኝነት መሆኑም ተገልጿል።
ከኮንትሮባንድ የጫት ምርቱ ጋር በቁጥጥር ሥር የዋሉት ስምንት የውጭ ሀገር ዜጎች ጉዳያቸው በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እየተጣራ ይገኛል።
መረጃውን ለኢዜአ የላከው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ህገ-ወጦችን ለመያዝ በተደረገው ኦፕሬሽን የጉሙሩክ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በቅንጅት መስራታቸውን ገልጿል።
የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ የሀገርን ጥቅምና ህልውና በሚፈታተኑ አካላት ላይ የሚደረገው ክትትል ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።
በመሰል የጥፋት ተልዕኮ ላይ የተሠማሩ ኃይሎች ከዕይታ ሊሰወሩ እንደማይችሉ ተረድተው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡
ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በመጠቆም ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የተለመደ ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡