ለውጭ አገራት የስራ ስምሪት የለማው መተግበሪያ በቀን ከ2 ሺህ በላይ ዜጎችን የማሰማራት አቅም የፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለውጭ አገራት የስራ ስምሪት የለማው መተግበሪያ በቀን ከ2 ሺህ በላይ ዜጎችን የማሰማራት አቅም የፈጠረ ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 2/2016 (ኢዜአ) ፦ ለውጭ አገራት የስራ ስምሪት አገልግሎት የለማውና "ብቁ" የተሰኘው መተግበሪያ በቀን ከ2 ሺህ በላይ ዜጎችን ለስራ ማሰማራት የሚያስችል አቅም መፍጠሩን የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የክህሎት ልማት፣ የኢንዱስትሪ ሰላም፣ መልካም የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት መፍጠርና የተቋም ግንባታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፤ ተቋሙ በተለይም የውጭ አገራት የስራ ስምሪትን ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ በኩል በተሳካ መልኩ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ አገራት የስራ ስምሪትን ፍትሓዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሰራር ስርአት መዘርጋቱን ጠቅሰዋል።
ለዘርፉ የስራ ክንውን የሚያግዝ "ብቁ" የሚል ስያሜ የተሰጠው መተግበሪያ ለምቶ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል።
በመተግበሪያው ለስራ ስምሪት የሚደረግ የምዝገባ ስርዓትን ጨምሮ የመረጃዎችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ ጭምር የላቀ አበርክቶ እያደረገ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
የዜጎች ደህንነት ተጠብቆ፣ ከአጭበርባሪዎችና ህገ ወጥ ደላሎች ይደርስ የነበረውን እንግልት አስቀርቶ በህጋዊ መንገድ ብቻ ውል ፈፅሞ ለመሰማራት የሚያስችል ጠቃሚ መተግበሪያ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም ለውጭ አገራት የስራ ስምሪት የለማውና "ብቁ" የሚል ስያሜ የተሰጠው መተግበሪያ በቀን ከ2 ሺህ በላይ ዜጎችን ለስራ የማሰማራት አቅም ፈጥሮልናል ብለዋል ሚኒስትሯ።
በአገር ውስጥ አምስት የስራ ቋንቋዎችን ጨምሮ ስድስት ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ያካተተ ዘመናዊ መተግበሪያ በመሆኑ ዜጎች በቀላሉ መገልገል እየቻሉ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
በውጭ አገር የስራ ስምሪት ከኢትዮጵያ ጋር ውል የገቡ አገራት ስምምነቶችን በአግባቡ እንዲተገብሩ የሚያስችልና አሰራርን ፍትሃዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ የሚያደርግ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ እድል፣ የሙያ ብቃት ማረጋገጫና የኢንተርፕራይዝ አገልግሎት መስጫ አዳዲስ መተግበሪያዎችን ይፋ ማድረጉም ይታወቃል።