ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የመድኃኒትና የህክምና ግብዓቶችን አቅርቦት ለማሻሻል የተደረገው ሪፎርም ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 1/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎችን አቅርቦትና ስርጭት ለማሻሻል የተደረገው ሪፎርም ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቡን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

አምስተኛው አገር አቀፍ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዓመታዊ ጉባኤ "ዘለቄታዊ አጋርነት ለማይበገር የጤና ግብዓት አቅርቦት ስርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ ተከናውኗል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ  የበሽታ ወረርሽኝ፣ የፀጥታ ችግር እና የፍላጎት መጨመር ለመድኃኒት አቅርቦትና ስርጭት ሰንሰለቱ ፈተና ሆነው ቆይተዋል።

በኢትዮጵያም ከዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች በተጨማሪ ውስጣዊ ችግሮች በመድኃኒትና የህክምና ግብዓት አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ይገለፃል፡፡

ውስጣዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችም እያሉ በ2015 በጀት ዓመት ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድኃኒቶች፣ ኬሚካሎች( ሪኤጀንቶች)፣ የሕክምና መገልገያና መሳሪያዎች ለጤና ተቋማት ተሰራጭተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በጉባኤው ላይ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለጤናው ዘርፍ የደም ስር ነው፡፡

አገልግሎቱ እንደ ሀገር በአይነትና በመጠን እያደገ የመጣውን የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያ ፍላጎት ለሟሟላት የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት መጨመር ጋር ተያይዞ የመድኃኒትና የህክምና ግብዓት አቅርቦት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በጤናው ዘርፍ የተደረገው ሪፎርም ፈተናዎችን ተቋቁሞ ተስፋ ሰጭ ለውጥ ማምጣት የተቻለበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የመድኃኒት የግዥ ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት ያስታወሱት ዶክተር ሊያ፤ በየደረጃው በተሰሩ የማሻሻያ ስራዎች የግዥ ሂደቱን የአሰራር ስርዓት ማስተካከል መቻሉን አብራርተዋል።፡

ለዚህ የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ከከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እስከ ባለሙያዎች  የተቀናጀ ተቋማዊ አሰራር የመጣ መሆኑን ገልጸው፤ ይሄ በቂ ባለመሆኑ ከዚህ በላይ መስራት ይገባል ሲሉም አስታውቀዋል።

መድኃኒት ከተገዛበት ጊዜ ጀምሮ ለአገልግሎት ከሚውልበት የህክምና ተቋም እስከሚደርስ ድረስ የሚከሰተውን ብክነት ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ የጤናውን ዘርፍ የህክምና ግብአቶችን ሳያሟሉ ለማዘመን መሞከር በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ይቆጠራል ብለዋል፡፡

ለዚህም በ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱ አሰራሮችን በማስተካከል የግዥ ስርዓቱን ማዘመን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ቆጠራ ማከናወን እና ለዓመታት የተጠራቀመውን ያልተወራረደ ሰነድ ማስተካከል ትኩረት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ግዢ መፈጸሙን ገልጸው፤ ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድኃኒት፣ የሕክምና መሳሪያ ስርጭት መከናወኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የአየርና የየብስ ትራንስፖርት አማራጮችን በመጠቀም  በአማራና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች  1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ግምት ያላቸው መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓቶች አሰራጭተናል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአገር ውስጥ አምራቾችን በማነቃቃት መድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ እገዛ እያደረገ መሆኑንም አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም