በቅድመ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ መስጫ ጣቢያዎች የሚስተዋለው የአሰራር ችግር እንዲስተካከል ተገልጋዮች ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
በቅድመ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ መስጫ ጣቢያዎች የሚስተዋለው የአሰራር ችግር እንዲስተካከል ተገልጋዮች ጠየቁ
አዲስ አበባ ፤ህዳር 1/2016(ኢዜአ)፦ የቅድመ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ በቴሌብር ከከፈሉ በኋላ የክፍያ ማረጋገጫ ለማግኘት ወደ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በሚሄዱበት ወቅት ያለው የአሰራር ችግር እንዲስተካከል ተገልጋዮች ጠየቁ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ የቅድመ ክፍያ የቆጣሪ አገልግሎት በቴሌብር የሚከፍሉ ደንበኞች በአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች የሚያጋጥማቸውን የሲስተም መቆራረጥ ችግር ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የቅድመ ክፍያ የቆጣሪ አገልግሎት ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቴሌብር መሰጠት መጀመሩ ይታወቃል።
ኢዜአ የአገልግሎት አሰጣጡን በተመለከተ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የቅድመ ክፍያ የቆጣሪ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን አነጋግሯል።
ተገልጋዮቹ እንደሚሉት የክፍያ ስርአቱ በቴሌ ብር መደረጉ ክፍያውን ሳይቸገሩ ባሉበት እንዲፈጽሙ አስችሏቸዋል።
ነገር ግን ክፍያ ከፈጸሙ በኋላ የክፍያ ማረጋገጫ ለማግኘት ወይም የቆጣሪ ካርዱን አክቲቬት ለማስደረግ ወደ ቅድመ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች በሚሄዱበት ወቅት ቀልጣፋ አገልግሎት እንደማያገኙና ለረጃጅም ሰልፎች እንደሚዳረጉ ተናግረዋል።
ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል አቶ ታምራት ተስፋዬ በቴሌብር ክፍያ ተፈጽሞ ወደ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የክፍያ ማረጋገጫ ለማግኘት በሚኬድበት ወቅት ያለው የአሰራር ችግር እስካልተቀረፈ ድረስ ክፍያ በቴሌ ብር መደረጉ ብቻውን ዋጋ የለውም ብለዋል።
አሰራር ዘመነ የሚባለው ተገልጋይ ባለበት ሆኖ ሁሉንም አይነት አገልግሎት በፍጥነት በእጅ ስልኩ ማግኘት ሲችል በመሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ወደዚህ አይነት አገልግሎት አሰጣጥ መግባት እንዳለበት ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ እቴነሽ ከበደ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ በሁሉም የእድሜ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ያማከለ መሆን እንዳለበት ገልጸው የግንዛቤ መፍጠር ስራውም ትኩረት የሚያሻው ነው ብለዋል።
ወይዘሮ ዮዲት ብርሃኑ በበኩላቸው የሲስተም ችግር ደንበኞች እንዲጉላሉ መንስኤ መሆኑን አንስተው የሚመለከተው አካል አሰራሩን ማስተካከል እንዳለበት ገልጸዋል።
የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለኢዜአ እንዳሉት ተቋሙ ከዚህ በፊት ወርሃዊ ፍጆታን ለመክፈል የሚባክነውን ጊዜ ለማስቀረት የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ተግባራዊ እያደረገ ነው።
በዚህም የንባብ ቆጣሪ የሚጠቀሙትን ጨምሮ የቅድመ ክፍያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ወደ ስርዓቱ እንዲገቡ መደረጉንና በዚህም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።
ይሁንና ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያቸውን በቴሌብር ከፈጸሙ በኋላ ወደ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች በሚመጡበት ጊዜ አልፎ አልፎ የሲስተም ችግር አጋጥሟቸው እንደሚመለሱ ነው አቶ መላኩ የገለጹት።
ተቋሙ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ደንበኞች ወደ አገልግሎት መስጫ ቦታ ሳይመጡ ባሉበት የክፍያ ስርዓቱን ማጠናቀቅ የሚችሉበትን አሰራር እየዘረጋ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በተያዘው ዓመት አሰራሩ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።