ቀጥታ፡

ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ የዳያስፖራ አባላት ያሉት ዓለም አቀፍ አማካሪ ቦርድ ሊቋቋም ነው 

አዲስ አበባ ፤ህዳር 1/2016(ኢዜአ)፦  ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ 250 የዳያስፖራ አባላት ያሉት ዓለም አቀፍ አማካሪ ቦርድ ሊቋቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በአገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ማጠናከር የሚያስችል ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ አካሒዷል።


 

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ እንዳሉት፤ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙና ለአገራቸው የተለያየ አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙ 250 የዳያስፖራ አባላት ተወካዮችን በመመልመል ዓለም አቀፍ አማካሪ ቦርድ ሊቋቋም ነው ። 

ቦርዱ በዋናነት ዳያስፖራው በአገሪቱ የትኛውም ጉዳዮች ላይ ያለውን ግንዛቤ እንዲያሰፋ የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውን ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በቅርቡ የሚቋቋመው ቦርድ መንግስት ለዳያስፖራው አባላት ያዘጋጃቸውን አማራጮች የማስረዳት፣ የማሳወቅና የማሳተፍ ስራዎችንም ይሰራል ነው ያሉት።

ይህም ዳያስፖራው ለአገሩ የሚያበረክተውን ሁሉን አቀፍ አስተዋጽኦ ለማጠናከር በእጅጉ የሚያግዝ እንደሆነም ዳይሬክተሩ  የተናገሩት።

ዳያስፖራው አገር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ መንግስት ያቀረበውን አገራዊ ጥሪ በመቀበል ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱ አይዘነጋም ብለዋል።

በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት የዳያስፖራው ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳትና ለማሳወቅ ባከናወናቸው ተግባራት ውጤት መገኘቱንም አንስተዋል።

በዋናነት የገንዘብ፣ የአይነትና የመሠረተ ልማት ድጋፎችን በማድረግ አለኝታነቱን ማረጋገጥ መቻሉንም እንዲሁ።

በአሁኑ ወቅትም ባለፉት ሶስት ወራት ዳያስፖራው ለህዳሴ ግድብ ግንባታና ለገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የሚውል የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረግ ችሏል ብለዋል።  

ይህንን ተሳትፎውን ይበልጥ ለማጠናከርና መንግስት የተለያዩ አማራጮችን በመዘርጋት ኃላፊነቱን እየተወጣ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የክልል ተጠሪ ተቋማት ዳያስፖራው በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴ ላይ የሚሳተፍበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና በማሳተፍ ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋልም ሲሉ አክለዋል።

ዲያስፖራው በመንግስት በኩል የተመቻቸለትን አማራጮች በመጠቀም የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክርም ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም