በሩብ ዓመቱ ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ስርጭት ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በሩብ ዓመቱ ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ስርጭት ተከናውኗል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 1/2016(ኢዜአ)፦ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድኃኒት፣ የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ስርጭት ማከናወኑን ኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ።
አምስተኛው አገር አቀፍ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዓመታዊ ጉባኤ "ዘለቄታዊ አጋርነት ለማይበገር የጤና ግብዓት አቅርቦት ስርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከናወነ ነው።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ እንዳሉት፤ በዓለም ላይ ባለፉት ሶስት ዓመታት በወረርሽኝና የፀጥታ ችግር ለመድኃኒት አቅርቦትና ስርጭት ፈተና ሆነው ቆይተዋል።
በኢትዮጵያም የጤና መድን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ54 ሚሊዮን በላይ ማደጉን ጠቅሰው፤ የቁጥሩ መጨመር በአቅርቦትና ስርጭቱ ላይ የራሱን ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።
ይህም ሆኖ በ2015 በጀት ዓመት ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድኃኒቶች፣ ኬሚካሎች( ሪኤጀንቶች) እና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች ለጤና ተቋማት መሰራጨቱን አመልክተዋል።
በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ግዢ መፈጸሙን አስረድተዋል።
በሩብ ዓመቱ ያለውን የመድሀኒት ክምችት ጨምሮ ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድኃኒት፣ የሕክምና መገልገያና መሳሪያዎች ስርጭት መከናወኑን ነው ዶክተር አብዱልቃድር ያስረዱት።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የአየርና የየብስ ትራንስፖርት አማራጮችን በመጠቀም መድኃኒቶችና ሌሎች የሕክምና ግብአቶችን የማሰራጨት ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
ግጭት በተከሰተባቸው በአማራና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ግምት ያላቸው መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓቶች መሰራጨቱን ጠቁመዋል።
አገልግሎቱ ለዓመታት ተጠራቅመው የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን በማስወገድ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል ።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአገር ውስጥ አምራቾችን በማነቃቃት መድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ እገዛ እያደረገ መሆኑንም አክለዋል።