ቀጥታ፡

የአፈር ብሎኬት አመራረት ቀላል ቴክኖሎጂ የአኗኗር ሁኔታን የመቀየር አቅም አለው

ሀዋሳ ፤ህዳር 1/2016 (ኢዜአ)..በሀገሪቱ በየአካባቢው የሚገኘውን እምቅ የማዕድን ሀብት ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር የሚያስችል የቀላል ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ጥረት መጀመሩን  የኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በአፈር ብሎኬት አመራረትና የቤት ግንባታ ክህሎት ያሰለጠናቸውን 30 ወጣቶች የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አስመርቋል።


 

ቴክኖሎጂውን ለማስፋፋት እንዲረዳ በወረዳው ያስገነባውን ሰርቶ ማሳያ ቤትም አስረክቧል።

በዚህ ወቅት የኢንስቲትዩቱ  ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጉታ ለገሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ተቋሙ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም ሀገሪቷ ያላትን ማዕድን ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ ነው።


 

ኢንስቲትዩቱ ዘርፉን በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሀብት፣ በፖሊሲና በአሰራር ሥርዓት አዳዲስ ሀሳቦችን በማምጣት ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል ።

የአፈር ብሎኬት ምርት የሙከራ ቴክኖሎጂ የዚሁ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ጠቁመው ቴክኖሎጂው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

በተለይ ባህር ዛፍን የሚተካ፣ የሴቶችንና የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተሳትፎ ያረጋገጠ ቀላል ቴክኖሎጂ ከመሆኑም ባሻገር የገጠር አርሶ አደሮች የኑሮ ሁኔታ ለመቀየር ወሳኝ ነው ያሉት ።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የልማት ስራዎች ለመደገፍ የሚረዳ ጠቃሚ ቴክኖሎጂ መሆኑንም ዶክተር ጉታ ጠቁመዋል። 

የሙከራ ቴክኖሎጂውን ስራ ላይ ለማዋል ከገዜ ጎፋ ወረዳ የአፈር ናሙና ተወስዶ በሀዋሳና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ላብራቶሪ ተመርምሮ አዋጭ፣ ውብና ጠንካራ ግንባታን ለማከናወን እንደሚያስችል በጥናት መረጋገጡን አስታውቀዋል።

በሃገሪቱ ያለውን እምቅ የማዕድን አቅም ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየርና ቴክኖሎጂውን ለማስፋፋት ተቋሙ የአምስት አመት ፕሮጀክት መንደፉን ገልጸዋል።

"በወረዳው 30 ወጣቶችን በትንሽ ሲሚንቶ የአፈር ብሎኬት ማምረት፣ ቤት መገንባትና በሥራ ፈጠራ ክህሎት ዙሪያ ሙያተኛ ቀጥረን በማሰልጠን ቴክኖሎጂውን አሸጋግረናል" ያሉት ዳይሬክተሩ በሀገሪቱ በብዙ አካባቢዎች ላይ ለቴክኖሎጂው ልማት ምቹ የሚሆን አፈር እንዳለ ተናግረዋል።


 

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ፋንታዬ በዞኑ ቴክኖሎጂውን ማዕከል ያደረገ ስራ ለመስራትና ወጣቶችን በስፋት ለማሰማራት አስተዳደሩ ይሰራል ብለዋል።

''ቴክኖሎጂን አክብደንና አርቀን ነው የምንመለከተው'' ያሉት አስተዳዳሪው ''ሆኖም ከትንሽ ነገር በመጀመር ትልቅ ነገር መስራት እንደሚቻል ይህ ቴክኖሎጂ በቂ ማሳያና ሞዴል ይሆነናል'' ብለዋል።

ከወረዳው ሰልጣኝ ወጣቶች መካከል ሀሳቡ ኃይሉ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ስራውን ከመጀመራቸው በፊት የአንድ ወር የተግባር ስልጠና በመውሰድ በአጭር ጊዜ ውጤታማ መሆናቸውን ተናግሯል።


 

አሁን ላይ በእኛ አቅምና ሙያ ደረጃውን የጠበቀ ቤት መስራት ችለናል የሚለው ወጣቱ ከጓደኞቹ ጋር "ንጋት የአፈር ብሎኬት አምራች ኢንተርፕራይዝ" በሚል ስያሜ በመደራጀት ቢዝነስ ውስጥ ለመግባት በሂደት ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።

በጎፋ ዞን የሣውላ ከተማ አስተዳደር ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አሰልጣኝ መምህር አትክልት ታደሰ በበኩላቸው ኮሌጁ በቀጣይ ቴክኖሎጂውን ለማባዛትና ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ በመስራት  የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።


 

ቴክኖሎጂው የኢነርጂ ኃይል የማይፈልግ፣ በትንሽ ስልጠናና በአካባቢው ከሚገኝ ግብዓት በቀላሉ የሚመረት በመሆኑ ወጣቶችና ባለሀብቶች በመስኩ ቢሰማሩ አዋጪ ቢዝነስ እንደሆነም አብራርተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም