ቀጥታ፡

ሥልጠናው ሀብትን ለይቶ በአግባቡ ለመጠቀምና ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አቅም ይፈጥራል 

ደሴ/ጎንደር ፤ ጥቅምት 30/ 2016 (ኢዜአ) ፡- ለመንግስት አመራር አባላት የሚሰጠው ሥልጠና ሀብትን ለይቶ በአግባቡ ለመጠቀምና ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አቅም ይፈጥራል ሲሉ የሥልጠና አስተባባሪዎች ገለጹ።

''ከዕዳ ወደ ምንዳ'' በሚል ርዕስ ለመንግስት አመራር አባላት የተዘጋጀው ሦስተኛ ዙር ስልጠና በኮምቦልቻና ጎንደር ከተሞች ዛሬ መሰጠት ተጀምሯል።

በኮምቦልቻ የሚሰጠውን የመራር አባላት ስልጠና አስተባባሪ አቶ ተተካ በቀለ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ለሌሎች አገራት የሚተርፍ እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና ጸጋ ቢኖራትም በአግባቡ አልምቶ መጠቀም ባለመቻሉ ከድህነት መውጣት አልተቻለም።

"በአገሪቱ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት አልምቶ በመጠቀም የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ አመራሩ ግንባር ቀደም ሆኖ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ለአመራሩ የአካባቢውን ሀብት ለይቶ መጠቀምና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል ነው ያሉት።

በኮምቦልቻ በተጀመረው ስልጠና ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የመንግስት አመራሮች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመው፤ "የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ብልጽግና ሚናቸውን ይወጣሉ" ብለዋል።

ሌላው የሥልጠናው አስተባባሪ ዶክተር ማማሩ አያሌው በበኩላቸ፤ ሥልጠናው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ህዳር 12 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይና ስለ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አመራሩ የበለጠ ግንዛቤ የሚጨብጥበት መሆኑን አመልክተዋል።

ሥልጠናው የተፈጥሮ ሀብትን ለይቶ ጥቅም ላይ በማዋል፣ በመልካም አስተዳደር ችግሮች አፈታትና ሀብት መፍጠርን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

"ሠልጣኞች በቆይታቸው በሚያገኙት እውቀትና ግንዛቤ ወደየአካባቢያቸው ሲመለሱ የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች በየደረጃው ሊፈቱና ሀብት ሊያመነጩ ይገባል" ብለዋል።

የአመራር አባላቱን አቅም በሥልጠና በማሳደግ ወቅቱን የሚመጥን፣ ሰላምና አንድነትን የሚያረጋግጥ አመራር ለመፍጠርም በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በጎንደር የሥልጠናው አስተባባሪ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል በበኩለቸው፤ አመራሩ በሥልጠናው ራሱን በማብቃት ለአገሪቱ የብልጽግና ጉዞ የበኩሉን አሻራ ይወጣል።

"አመራሩ በሥልጠናው በሚያገኘው እውቀትና ክህሎት ዘመኑን የዋጀ አመራር በመስጠት ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል" ሲሉም አክለዋል።

ሥልጠናው አመራሩ የጋራ የሃሳብና የአመለካከት አንድነት በመያዝ ለአገረ መንግስት ግንባታና ለዴሞክራሲ መጠናከር ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሚናውን ለመወጣት ራሱን የሚያዘጋጅበት መሆኑንም አስታውቀዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም