ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር ትልቅ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው-የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር ትልቅ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው-የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 30/2016 (ኢዜአ) ፦ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለቀጣናዊ ትስስር ትልቅ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት መሆኑን ተቀማጭነታቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ገለጹ፡፡
ተቀማጭነታቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።
ወታደራዊ አታሼዎቹ ግድቡ በኢትዮጵያውያን እየተገነባ የሚገኝ ቁልፍ የልማት መሳሪያ እና የህዝቦች የኩራት ምልክት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዚህም ከኢትዮጵያ ባለፈ ለቀጣናው አገራት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሱዳን ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴር ጀነራል አብደልመጀድ አናስ፤ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባለፈ የአፍሪካ ኩራት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሱዳንን ጨምሮ ለቀጣናው አገራት ብርሃን የሚሰጥና ጉርብትናን የሚያጠናክር ፕሮጀክት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ምክትል ወታደራዊ አታሼ ሌተናል ኮሎኔሌ ኦፑል ቻም ኦጂሉ፤ ደቡብ ሱዳን ከግድቡ ትሩፋት ተጠቃሚ ከሚሆኑ አገራት አንዷ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
በጉብኝታቸው ወደ ታችኛው ተፋሰስ አገራት ውሃው በተገቢው ሁኔታ እየፈሰሰ መሆኑን መመልከታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ግድቡ የትኛውንም አገር እንደማይጎዳ በተግባር እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡
ግድቡ ቀጣናውን በኃይል በማስተሳሰር ኢትዮጵያንና ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን የኢኮኖሚ እድገት ለማሳለጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።
በአፍሪካ ህብረትና በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ ወታደራዊ ጉዳዮች ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል ዳንኤል ማይክ ጁሌት በበኩላቸው ግድብ ታዳሽ ኃይል የሚያመነጭ መሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ካናዳ በታዳሽ ሃይል ልማት ዘርፍ የካበተ ልምድ እንዳላት ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያን የውሃ ሃብቶቿን በማስተዳደር በኩል አበረታች ስራ እያከናወነች ስለመሆኑ አውስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የናሚቢያ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ኤር ኮሞዶር ማኬንዚ ማንፍሬድ፤ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ገንዘብ አውጥተው ለነገ ትውልድ የሚገነቡት ትልቅ ፕሮጀክት እንደሆነ አንስተዋል።
ይህም ከድህነት የሚያላቅቅና ሌሎች የቀጣናውን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ውህደት የሚያፋጥን መሆኑን ተናግረዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ታላቅና የሚያስደንቅ ፕሮጀክት ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል ማርኮ ፖዲ ናቸው።
ግድቡ በጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ የሚገነባ መሆኑም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያጠናክርና የትበብራቸው ቋሚ መገለጫ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴር ጀኔራል ሻሪፉል ኢስላም፤ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ትልቅ መሠረት የሚሆን ነው ብለዋል።
የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ የጉብኝቱ ዓላማ ኢትዮጵያ በራሷ ጥራት የትኛውንም ሀገር ሳትጎዳ እየገነባች መሆኗን እውነታውን እንዲገነዘቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያን ከድህነት ለመውጣት ሙሉ አቅማቸውን አሟጠው በመጠቀም እየገነቡት የሚገኝ ግድብ መሆኑንም ለአታሼዎቹ ማስረዳት ተችሏል ነው ያሉት።