ቀጥታ፡

በግል ንፅህና መጓደል ምክንያት የሚመጣ ሞትና ህመምን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ሊያግዝ ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 30/2016 (ኢዜአ) ፡- በግል ንፅህና መጓደል ምክንያት የሚመጣ ሞትና ህመምን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ሊያግዝ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ጤና ሚኒስቴር “ከታጠበ እጃችን ይጠበቃል ጤናችን” በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም የእጅ መታጠብ ቀን በኢትዮጵያ ለ12ኛ በዓለም ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ ዛሬ አክብሯል። 

ቀኑ እጅን በአግባቡ በሣሙናና በውሃ በመታጠብ ከተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች የፀዳና ጤናው የተጠበቀ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሚቻል አጉልቶ ለማሳየትና ለጤናማ ሕይወት መሠረት መሆኑን ለማስገንዘብ ታስቦ እንደሚከበር ተገልጿል። 


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ዕለቱን አስመልክተው እንደገለጹት፤ በንፅህና መጓደል ምክንያት የሚመጣ ሞትና ህመምን ለመቀነስ የሚያግዝ ስራ መስራት ያስፈልጋል።

ተቅማጥ፣ ኮሌራ፣ የመተንፈሻ አካላትን የመሳሰሉ በሽታዎችን በዋናነት መከላከል የሚቻለው የግልና የአካባቢ የጤና አጠባበቅ ሥርዓትን በመተግበር እና የእጅ ንጽሕናን በመጠበቅ መሆኑን ጠቁመዋል። 

እጅን በውሃና በሣሙና በመታጠብ ተቅማጥን ከ50 በመቶ አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት በሽታ (ኒሞኒያ) ከ25 በመቶ በላይ በመቀነስ የህፃናትን ሕይወት መታደግ እንደሚቻል ገልፀዋል።

ተቅማጥ እና አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት በሽታ (ኒሞኒያ) በንጽህና ጉድለት የሚመጣ ሲሆን፤ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት በከፍተኛ መጠን እየጎዳ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የእጅ መታጠብን ባህል ከፍ ለማድረግ በጤና ኤክስቴንሽን መርሃ-ግብር ውስጥ በማካተት እየተሰራ ነው።

በኢትዮጵያ “የእጅ ንጽሕና ለሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገሪቱ ተሞክሮ መቅረቡን ገልፀዋል።

ብሔራዊ ፍኖተ ካርታውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ሁሉም አካላት ድርሻቸውን አውቀው ርብርብ እንዲያደርጉ ዶክተር ደረጀ አሳስበዋል።

በተለይ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ወላጆችና የየአካባቢው ህብረተሰብ በግል ንፅህና መጓደል ምክንያት የሚመጣ ሞትና ህመምን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት በተቀናጀ ሁኔታ ሊያግዙ ይገባል።   


 

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ ትምህርት ቤቶች ምቹ የመማር ማስተማር ሥፍራ እንዲሆኑ ንጹህ የመጠጥ ውሃና መፀዳጃ ቤት እንዲኖራቸው በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።  

ከዚህም በተጨማሪ 24 ሚሊየን የሚጠጉ ተማሪዎች አካታች የጤና አጠባበቅ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ።

በጤና ዙሪያ የሚሰሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት በዘላቂነት ከንጽህና ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።


 

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑ በሽታዎች ከንፅህና ጉድለት የሚመጡ ሲሆን ከ23-40 በመቶ የሚሆነውን ሞትና ህመም እጅን በመታጠብ መከላከል ይቻላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም