ኢትዮ-ቴሌኮም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ለማገዝ የሚያስችለውን መርሃ-ግብር ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ-ቴሌኮም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ለማገዝ የሚያስችለውን መርሃ-ግብር ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 30/2016 (ኢዜአ) ፡- ኢትዮ-ቴሌኮም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ ለማገዝ የሚያስችለውን መርሃ-ግብር ይፋ አደረገ።
መርሃ-ግብሩ ''ዘላቂ የጋራ ማኅበራዊ ኃላፊነት ለወገን ብሩህ ተስፋ '' በሚል መሪ ቃል ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ኢትዮ-ቴሌኮም ዛሬ የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ ዘላቂ የሆነ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸውን መርሃ-ግብር ነው ይፋ ያደረገው።
የኢትዮ-ቴሌኮም የኮሙኒኬሽን ኤክስኪውቲቭ ኦፊሰር መሳይ ውብሸት በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ድርጅቱ የተለያዩ ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት የሚያስችሉትን ዕቅዶች ነድፎ እየሰራ ነው።
ከዚህ ውስጥም የበጎ አድራጎት ተቋማት በቴሌኮሙና በራሳቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቅመው ገንዘብ ማግኘት የሚያስችላቸውን አሠራር ነው ዛሬ ይፋ ያደረገው።
በዚህ መሠረትም በማህበራዊ እና በሰብዓዊ ሥራቸው ውጤታማ የሆኑ የበጎ አድራጎት ተቋማትን በጥናት በመለየት ማኅበረሰቡን የማገዝ ሥራቸውን በዘላቂነት እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም የተመረጡ ተቋማት ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፣ ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ካንሰር አሶሴሽን፣ ባቡልኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት፣ መቄዶኒያ አረጋውያን መርጃ ማዕከል፣ ሙዳይ በጎ አድራጎትና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ናቸው።
እነዚሁ ተቋማት ከ 2 ሚሊዬን በላይ ተከታይ ባለው የቴሌኮሙ የማኅበራዊ ሚዲያና የራሳቸው ገፆች ላይ አንድ ተከታይ ሲኖራቸው 30 ብር የሚያገኙ ይሆናል ነው የተባለው።
በተጨማሪም የበጎ አድራጎቶቹ ተግባር በተለያየ ገፆች ሲጋሩ ወይም ሼር ሲደረጉ 10 ብር የሚያገኙ ሲሆን፤ ቴሌኮሙ ደግሞ ባገኙት አጠቃላይ ገቢ ላይ 10 በመቶ ጨምሮ የሚከፍላቸው ይሆናል ነው የተባለው።
በመሆኑም የተመረጡት ስምንት ድርጅቶች ከኅዳር እስከ ሰኔ ባሉት ወራት ውስጥ ተደልድለው የጀመሩትን ማኅበራዊ ኃላፊነቶች እንዲወጡ የሚያደርግ ገቢ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት በጎ ፈቃደኞችና የግብረ-ሰናይ ድርጅቶቹ አምባሳደሮች በበኩላቸው፤ ተቋሙ እያደረገ ያለው ድጋፍ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መሥራች ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ትልልቅ ተቋማት ከኢትዮ- ቴሌኮም ልምድ በመውሰድ ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ማገዝ ይችላሉ ነው የሚሉት።
ኢትዮ-ቴሌኮም በመላው ሀገሪቱ የሞባይል ተጠቃሚ ከ73 ሚሊዬን በላይ፣ የቴሌ ብር ደግሞ ከ37 ሚሊዬን በላይ ደንበኞች እንዳሉት ይታወቃል።