ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕጩ ሰብሳቢ ጥቆማ ከህዳር 3 እስከ 13 ቀን 2016 ዓ᎐ም ድረስ ይከናወናል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 30/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕጩ ሰብሳቢ ጥቆማ ከመጪው ሰኞ ከህዳር 3 እስከ 13 ቀን 2016 ዓ᎐ም ድረስ እንደሚከናወን የሥራ አመራር ቦርድ መልማይ ኮሚቴ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራ አመራር ቦርድ መልማይ ኮሚቴ ወደ ሥራ መግባቱን እና የጥቆማ ሂደቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራ አመራር ቦርድ መልማይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ ታጋይ ታደለ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 5/1 ዕጩ የስራ አመራር ቦርድ አባላት መልማይ ኮሚቴ መቋቋም እንዳለበት ይደነግጋል ብለዋል።

በዚህ መሰረትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ስምንት አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ዕጩ መልማይ ኮሚቴ መሰየማቸውን አስታውሰዋል።

በዚሁ መነሻነትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ዕጩ መልማይ ኮሚቴው በይፋ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

መልማይ ኮሚቴውም ከኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ከሳይንስ አካዳሚ፣ ከሰራተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን፣ ከንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ ከሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን፣ ከሲቪል ማህበራትና የሀገር ሽማግሌዎች የተውጣጣ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁንም የውስጥ አሰራር መመሪያ በማውጣት፣ የአፈፃጸም ድርጊት መርሃ-ግብር የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት እና የዕጩዎች መመልመያ መስፈርቶችን እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።

በጥቆማ የሚቀርቡ እጩዎችም በዜግነት ኢትዮጵያዊ፣ ገለልተኛ፣ ሙያዊ ብቃት፣ መልካም ስነ-ምግባር፣ ኃላፊነትን የመሸከም ብቃት፣ ፍቃደኝነትና ተዓማኒነት እና የመምራት ክህሎት ያላቸው መሆን እንዳለባቸው በመስፈርቱ መቀመጡን ገልጸዋል።

በኢ-ሜይል erc@hopr.gov.et ፣ ዋትስአፕና ቴሌግራም +251987141100፣ በፖስታ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራ አመራር ቦርድ መልማይ ኮሚቴ በፖ.ሳ.ቁ. 80001 እና በአካል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመቅረብ ጥቆማ መስጠት የሚቻል መሆን አመላክተዋል።

ጠቋሚዎችም ለጥቆማ በተዘጋጀው ወረቀት ላይ የተቀመጡ መገለጫዎችን በመሙላት ከመጪው ሰኞ ህዳር 3 ቀን 2016 ከጥዋቱ 2፡30 ጀምሮ እስከ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ድረስ ለመልማይ ኮሚቴው ጥቆማ ማቅረብ እንደሚቻል አስታውቀዋል።

ከላይ ከተቀመጠው የቀንና የሰዓት ገደብ ውጪ የሚመጡ ጥቆማዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እጩ ሰብሳቢ ሥራ አመራር ቦርድ መልማይ ኮሚቴ ሰብሳቢው አንስተዋል።

መልማይ ኮሚቴው የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣም ኢትዮጵያውያን፣ የፖለቲካ ድርጀቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች ተቋማት በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም