ቀጥታ፡

የግብርና ግብዓት አቅርቦት በስፋት ተደራሽ እየተደረገ ነው

አዳማ ፤ ጥቅምት 30/2016 (ኢዜአ) ፡- በግብርና ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የግብርና ግብዓት አቅርቦት በስፋት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ላይ በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በውይይቱ ላይ ግብርናን ለማዘመንና በዘርፉ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የግብርና ግብዓቶችን በአግባቡ ለአምራች አርሶ አደሮች ተደራሽ የማድረግ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደገለፁት፤ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በወቅቱና ጊዜውን በጠበቀ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው።

ለ2015/16 ዓ.ም የምርት ዘመን የማዳበሪያ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ መጨመር፣ የተንዛዛ የግዥ አሰራርና በወቅቱ ያለመግዛት በፈጠረው ችግር የአፈር ማዳበሪያ ተደራሽ ማድረግን ፈታኝ አድርጎት ነበር ብለዋል።

በዘንድሮው ዓመት በተለይ ለ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የሚገዛበትን ወቅትና መመሪያ በማሻሻል በአሁኑ ወቅት 13 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በመፈፀም ወደ ሀገር ውስጥ የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

''በአሁኑ ወቅት ሁለት መርከቦች በጂቡቲ ወደብ የአፈር ማዳበሪያ እያራገፉ ነው'' ያሉት ዶክተር ግርማ ወደ ሀገር ውስጥ የማጓጓዝ ስራ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።


 

ባለፈው የበጀት ዓመት የተገዛውን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ በማጓጓዝና ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ሂደት ላይ ሰፊ ክፍተት ነበር ያሉት ሚኒስትሩ ዘንድሮ የተንዛዛና የተራዘመ የግዥ ሂደትን በማስቀረት የተፋጠነ ግዥ መከናወኑን ተናግረዋል።

ብሔራዊ ባንክ፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽንና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አባል የሆኑበት ቦርድ በማዋቀር በአዲሱ መመሪያ መሰረት ግዥ መከናወኑን አመልክተዋል።

ሚኒስቴሩ በግብርና ዘርፍ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የግብዓት አቅርቦትን በስፋት ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ በበኩላቸው የማዳበሪያ ስርጭትን በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ የማጓጓዝ ስራው ትኩረት ማግኘቱን ገልጸዋል።


 

''ማዳበሪያ በጊዜው ለተጠቃሚው አርሶ አደር ማድረስ መቻል ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ አለብን'' ያሉት ዶክተር ዓለሙ ''አምና በማጓጓዝ ላይ የገጠመን ችግር ፈፅሞ አይደገምም'' ነው ያሉት።

ለዚህም ምንም ምክንያት ማቅረብ አያስፈልግም ያሉት ዶክተር አለሙ ማዳበሪያውን ከተገዛበት ቦታና ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥና ወደ አርሶ  አደሩ የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስን ጨምሮ የረጅም የጭነት ማመላለሻ አገልግሎት ድርጅቶችና የባቡር ስምሪት በመስጠት ከወደብ የማንሳት ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በመድረኩ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም