ቀጥታ፡

ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች-አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ

ዲላ፤  ጥቅምት 30/2016 (ኢዜአ) ፡- የፈረንሳይ መንግስት ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ገለጹ።

በአምባሳደሩ የተመራ የልዑካን ቡድን የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር አካል የሆኑትን የትክል ድንጋይ መካነ ቅርሶችን ተዘዋውረው ጉብኝተዋል።

አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ከአንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ትስስርና ወዳጅነት ያላቸው ሃገራት ናቸው።


 

በተለይ በቅርስ ጥበቃ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርሲቲያናትን ጨምሮ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የዓለም ቅርሶች ተጠብቀው እንዲቆዩ የፈረንሳይ መንግስት አስፈላጊው እገዛና ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የስነ ቅርስ ተመራማሪዎችም የጌዴኦን ባህላዊ መልክዓ ምድር የስነ ቅርስ ጥናትና ምርምር እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የዓለም አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ድጋፍና ትስስር ማዕቀፍ አካል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ሃብት መሰረት የሚሆኑ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን ያነሱት አምባሳደሩ ብዝሃ መስህብ የሆነው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር አንዱ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም የመስህብ ሃብቶችን በማልማት ለኢኮኖሚ እድገት መጠቀም እንደሚገባ ጠቅሰው ለዚህም ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ መስህብን የመጠበቅ ስራን ማጠናከር ይጠይቃል ብለዋል።


 

ቅርሱ ተጠብቆ እንዲቆይ ያለበትን ደረጃ በምርምር የመለየት ስራ ''ከፈረንሳይ አባያ ሚሽን ፕሮጀክት'' ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ጉብኝቱም ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የሚዳሰስና የማይዳሰስ መስህብን በአንድ ላይ አቅፎ የያዘው የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር በአፍሪካ ከሚገኙ መስህቦች ለየት እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

ይህም ሰውና ተፈጥሮ ተስማምቶ የመኖር ጥበብ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ "የሰው መብዛት የዛፍ መብዛት" የሚለው መርህ ለአረንጓዴ አሻራ ልማታችን ትልቅ አቅምና ተሞክሮ የሚሆን ባህላዊ ስርዓት መሆኑን አስረድተዋል።

መስህቡ እንዲጠበቅ ባህላዊ ስርዓትን ከማጠናከር ባለፈ የምርምር ውጤቶችን ለመተግበር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከሰላሳ ዓመት በፊት ጌዴኦ በምስራቅ አፍሪካ የትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ ክምችት ማዕከል መሆኑን በስነ ቅርስ ጥናትና ምርምር ያረጋገጡት የፈረንሳይ ባለሙያዎች መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ናቸው።


 

''ዛሬም ሀገሪቱ በዘርፉ እያካሄደች ያለውን ጥናትና ምርምር የዞኑ አስተዳደርና ህዝብ ዕውቅና የሚሰጠው እንዲሁም በትልቅ ምስጋናና አክብሮት የሚመለከተው ነው'' ብለዋል።

የጌዴኦን ባህላዊ መልከዓ ምድር ወካይ የመስህብ ስፍራዎችን በመንገድ መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ከሀገር ውስጥና ከውጭ ተቋማት ጋር በትስስር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ለማስፋት በጥምር እርሻ፣ በቡናና መስህብ ቱሪዝም ዘርፎች የግል ባለሃብቱን ተሳትፎ ለማሳደግ የአጭር ጊዜ የዕቅድ ማዕቀፍ ተዘጋጀቶ ወደ ትግበራ መገባቱን ጠቅሰዋል።

የልዑካን ቡድኑ የቱቲፈላ፣ የጨልባ ቱቲቲ እና የሰደይ መርካቶ የትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ ስፍራዎችን የተጎበኘ ሲሆን በጉብኝቱንም የዘርፉ የዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችና የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም