የህግ የበላይነት የተረጋገጠባትና ፍትህ የሰፈነባት ሀገር እውን ለማድረግ የፍትህ አካላት አቅም ግንባታ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው

አዳማ፤ጥቅምት 30/2016 (ኢዜአ):-የህግ የበላይነት የተረጋገጠባትና ፍትህ የሰፈነባት ሀገር እውን ለማድረግ የፍትህ አካላት አቅም ግንባታ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ገለፁ ።

የፌዴራልና የክልሎች የህግና ፍትህ አካላት አመራሮችና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ወቅት ''በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የፍትህ ስርዓት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ችግሮችን መለየት ቀዳማዊ ስራችን መሆን አለበት'' ብለዋል።

እነዚህ ችግሮች ከተለዩ በኋላ የፍርድ ቤቶችን አቅም መገንባት፣ የህግ ሙያተኞች የአቅም፣ ክህሎትና ዕውቀት ክፍተት ለመሙላት በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

ወደ ፍትህ ተቋማት የሚመጡ የህግ ተመራቂዎች መሰረታዊ የፍትህና የህግ ክህሎት፣ ዕውቀትና ስነ-ምግባር እንዲኖራቸውም ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል።

በተለይም ከፍትህና ህግ ኢንስቲትዩቱ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥና በፍትህ ስርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለማስወገድ የተጀመረው ስራ ይጠናከራል ብለዋል።

በዚህም የህግ የበላይነትና ፍትህ የሰፈነባት ሀገር እውን በማድረግ የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ የአቅም ግንባታ ስራዎች በስፋት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የህግና የፍትህ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚሰጡት ስልጠናዎች በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለውጥ የሚያመጡ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የፌዴራል የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የፍትህ አካላት አቅም ግንባታና ስልጠና ዙሪያ ያሉ ክፍተቶች፣ የአሰራርና የህግ ስርዓት ጥናቶች ሲያካሄድ መቆየቱን አንስተዋል።


 

በተጨማሪም የህግ መዝገበ ቃላት ጥናት፣ የፍትህ አሰጣጥና የህግ ታራሚዎችን መልሶ ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀል ዙሪያ በርካታ ጥናቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመትም ኢንስቲትዩቱ በፍትህ ስርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስወገድ የሚያግዙ የፍትህና ህግ አሰራር፣ በዳኞችና የፍትህ አካላት ስነ-ምግባርና የዳኝነት ነፃነት ዙሪያ ትኩረት ያደረጉ የጥናትና አቅም ግንባታ ስራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

በዛሬው የውይይት መድረክም የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመቅረፍ የሚያግዙ የአቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ብለዋል።

አምባሳደር ደግፌ፣ የፍርድ ቤቶች የስልጠና አካሄድ ወጥነት ባለው መልኩ በፌዴራልና በክልል እንዲሰጥ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም