ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ከቻይና በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ጋር በትብብር ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ  ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ከቻይና በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ጋር በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መቆጣጠር ላይ በትብብር ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ  ተወወያይተዋል።

እ.ኤ.አ በ2022 የተደረገው የጋራ መግባቢያ ስምምነት በሁለቱ ተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ፣ የተላላፊ በሽታዎች መከላከልና ቁጥጥር የሰው ሀይል ሥልጠና፣ የላብራቶሪዎች አቅም ግንባታ እና የህብረተሰብ ጤና ምርምር ስራዎችን በጋራ ለማከናወን የሚያስችል መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ እንዳሉት ስምምነቱ በህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር፣ በቅድመ ዝግጅት በቅኝትና ምላሽ ስራዎች፣ በተላላፊ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው ። 


 

በእናቶች እና ህጻናት ጤና፣ በስርአተ ምግብ እና የምግብ ሳይንስ፣ ለህብረተሰብ ጤና ስጋት የሆኑ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ በሽታዎች ምርምር ላይ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መቆጣጠር ላይም በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል።

የኢንስቲትዩቱ ባለሞያዎች ወደ ቻይና ሄደው ስልጠና መውሰዳቸውንና ባለሞያዎቹ ያገኙትን ትምህርትና ልምድ በመተግበር ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ሁለቱ ተቋማት በትብብር የሚሠሩ ስራዎች ይቀጥላሉ ብለዋል።

የቻይና ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር  ፕሮፌሰር ሼን ሆንግቢን በበኩላቸው በሁለቱ ተቋማት መካከል መደበኛ ትብብርን ለመመስረት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን አንሰተዋል።

በተላላፊ በሽታዎች መከላከልና ቁጥጥር የልምድ ልውውጥ መደረጉንም  ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም