በሲዳማ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎትን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎትን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ ነው
ሀዋሳ፤ ጥቅምት 30/2016 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎትን ተደራሽ ለማድረግ ጠንካራ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ሲዳማ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በአገልግሎቱ የሲዳማ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽህፈት ቤት የሪጅናል ዲስትሪክት የኮንስትራክሽና የጥገና ሂደት ኃላፊ አቶ አንተነህ ጠለለው ለኢዜአ እንዳሉት ተቋሙ በክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎትን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ጽህፈት ቤቱ አገልግሎቱን አስተማማኝ፣ ፍትሀዊና ተደራሽ ለማድረግ ሰፊና ጠንካራ የለውጥ ስራዎችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለመልሶ ግንባታ፣ ለቅድመ መከላከልና ለአዳዲስ መጋቢ መስመሮች ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም በተሰራው የቅድመ መከላከል ተግባር በንሳ ዳዬ አካባቢ 12 ሜትር ርዝመት ያላቸው 164 የእንጨት ፖሎች መተከላቸውን አቶ አንተነህ ገልፀዋል።
''ኤሌክትሪክ ዛሬ ላይ መሰረታዊ የሀገር ኢኮኖሚ ምንጭ እየሆነ መጥቷል'' ያሉት አቶ አንተነህ በተለይ ኢንዱስትሪዎች፣ የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት በአገልግሎቱ ላይ ጥገኛ በመሆናቸው ተደራሽነቱን አስተማማኝ፣ ፍትሃዊና የተሳለጠ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል።
በመሰረተ-ልማት ላይ በሚደርስ ስርቆት፣ በአደጋና በማከፋፈያ መስመር እርጅና ምክንያት እየተከሰተ ያለውን የኃይል መቆራረጥ በዘላቂነት ለመፍታት በመንግሥት የ77 ሚሊዮን ብር በጀት ሰባት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት መታቀዱን አስረድተዋል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል የአርቤጎና ከተማ የሳውዝ ስፕሪንግ ፕላንት ማናጀር አቶ ሞላልኝ ወርቅዬ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በከተማዋ የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ፋብሪካው በጄኔሬቴር ሲጠቀም መቆየቱን አውስተዋል።
የነዳጅ ዋጋ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ሲቸገሩ እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሙሉ በሙሉ ባይፈታም አንጻራዊ የሆነ መሻሻል ማሳየቱንና ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
የአርቤጎና ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ዘርፌ አበባየሁ እና የበንሣ ዳዬ ከተማ ነዋሪው አቶ ዳንኤል ቦራ በሰጡት አስተያየት ምንም እንኳ የሀይል መቆራረጥ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም አሁን ላይ መጠነኛ መሻሻሎች እንዳሉ ተናግረዋል።