ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ሕብረት ሲምፖዚየም በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ሕብረት ሲምፖዚየም በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30/2016 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ሕብረት 386ኛ ሲምፖዚየሙን ከሕዳር 3 ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በአዲስ አበባ ያካሂዳል።
ሲምፖዚየሙ "የጥቁር ሰማይና የስነ-ፈለክ ቅርሶችን አስትሮ ቱሪዝምን ለማሳደግ ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ የሚከናወን ነው።
ሲምፖዚየሙን የዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ሕብረት (IAU) ከስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጋራ በመተባበር ያዘጋጁታል።
ተቋማቱ ከሕዳር 3 እስከ 7 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚያካሂዱትን ሲምፖዚየም አስመልክቶ ለኢዜአ መግለጫ ሰጥተዋል።
በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢኒስቲትዩት የቀጣናዊ ትስስር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አለምዬ ማሞ እንዳሉት፤ ሲምፖዚየሙ የሕዋ ሳይንስ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ከሚያደርገው አስተዋጽኦ ባሻገር የስነ- ፈለክ ጥናት (astronomy) የቱሪዝም አቅምን ለመጠቀምና የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ማስተዋወቅ አላማ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚታዩ ከዋክብቶችና ፕላኔቶች (dark sky)፣ ከዋክብቶች የሚታዩበት መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ፣ምቹ የሆነ የአየር ፀባይና ቴሌስኮፕን ጨምሮ ከዋክብቶቹን ለማየት የሚውሉ ቁሶች እንደ ስነ- ፈለክ ቅርሶች እንደሚቆጠሩ አመልክተዋል።
ከዚህ አንጻር የስነ- ፈለክ ቱሪዝም ላይ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ዘርፉን ማልማትና ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና ምቹ አየር ጸባይ ለስነ- ፈለክ ቱሪዝም እምቅ አቅም እንዳላት የሚያሳይ መሆኑን አቶ አለምዬ አስረድተዋል።
በላሊበላ የፀሐይ ግርዶሽን ጨምሮ በምሽት ከዋክብቶችን የማየት ልምድ እንዳለ ጠቅሰው፤ የባሌ ተራሮች፣ ወላይታ ዳሞታ ተራራና አርባ ምንጭ አካባቢ የስነ- ፈለክ ቱሪዝም እምቅ አቅም ካላቸው ቦታዎች ይጠቀሳሉ ብለዋል።
ሲምፖዚየሙም ኢትዮጵያ በስነ- ፈለክ ቱሪዝም ያሉ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማየት ዘርፉን የማልማት ተሞክሮ ለማግኘት ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር የማይስ ቱሪዝም የሽያጭ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ብዙዓለም ጌቱ በበኩላቸው የስነ -ፈለክ ቱሪዝም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልዩ የሆነ የቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ የሚካተት መሆኑን ገልጸዋል።
ዘርፉ ለኢትዮጵያ አዲስ እንደ መሆኑ የጉባኤው መካሄድ ኢትዮጵያ በቀጣይ የስነ- ፈለክ ቱሪዝም አቅም ወደ ቱሪዝም ምርት በመቀየር የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ማግኘት የምትችልባቸውን አማራጮች ለመመልከት እንደሚያስችላት ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ ከጉባኤው የሚያገኛቸውን ዓለም አቀፍ ልምድ ለዘርፉ ልማት ስራዎች እንደሚጠቀምባቸውም አመልክተዋል።
የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ሕብረት 386ኛ መደበኛ ስብስባ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የስነ- ፈለክና አስትሮፊዚክስ ፕሮፌሰር ሚሪያና ፖቪች ጉባኤው ኢትዮጵያ በስነ- ፈለክ ዘርፍ እያከናወነች ያለው ስራ ትኩረት እንዲያገኝና ድጋፍ እንድታገኝ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት በስነ- ፈለክ ቱሪዝም ያላቸውን አቅም በመጠቀም ዘርፉን የማልማትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መፍጠር ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከሲምፖዚየሙ ቀደም ብሎ ሕዳር 1 እና 2 2016 ዓ.ም ዲጂታል ቱሪዝምን ማስፋፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ አህጉራዊ የጠፈር አሰሳ አውደ ጥናት ይካሄዳል።
በተጨማሪም በሁለቱ ቀናት በቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰሩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ አስጎብኚዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት የስነ- ፈለክ(Astronomy) ቱሪዝምን የተመለከተ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥም ተመላክቷል።
በሲምፖዚየሙና በአውደ ጥናቱ ላይ ከ200 በላይ ከአፍሪካ፣እስያና አውሮፓን ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚመጡ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ሕብረት ሲምፖዚየም ስታዘጋጅ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ በፊት አንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2019 356ኛውን የሕብረቱን ሲምፖዚየም ማስተናገዷ የሚታወስ ነው።
እ.አ.አ በ1919 የተቋቋመው ዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ሕብረት ኢትዮጵያን ጨምሮ 85 አባል አገራት አሉት።