የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን በትውልድ ስብዕና ግንባታ ላይ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል - አቶ ብናልፍ አንዱዓለም - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን በትውልድ ስብዕና ግንባታ ላይ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል - አቶ ብናልፍ አንዱዓለም
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ)፡- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን በትውልድ ስብዕና ግንባታ ላይ በመስራት ለጠንካራ አገረ መንግስት ግንባታ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ፡፡
"የሀገር ግንባታ መሠረታውያን" በሚል መሪ ሃሳብ የሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋራ ያዘጋጁት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩም ለኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት መሳካት የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
የሀገረ መንግስት ግንባታ ስራ በአንድ ጊዜ የሚያልቅ ባለመሆኑ ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር በኩል የሁሉም ዜጋ አደራ ሊሆን ይገባል ተብሏል።
የሀገረ መንግስት ግንባታን ለማሳካት የጋራ ማንነትን መገንባት፣ ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ እና ብሔራዊ እሴቶች ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግም በመድረኩ ተገልጿል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የምናስባትንና የምንመኛትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ከምንም በላይ ህብረ-ብሔራዊነት መሰረት ያደረገ አገራዊ አንድነት መፍጠር ይገባል ብለዋል።
ሁሉም ማንነቶች መከበር አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ በእኩልነትና በፍትህ ሁሉም ማንነቶች ተቀባይነት ማግኘት እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
ከማንነት መሰረት በመነሳትም ሁሉንም የሚያስተሳስረውን ኢትዮጵያዊ ማንነት እና ብሔራዊነት መገንባት ይገባል ነው ያሉት።
የዚህ ዘመን አርበኝነት መሆን የሚገባውም ሁሉን ሊያሥተሳስር የሚችል የወል ትርክት መፍጠር ሲቻል ነው ብለዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለስኬታማ አገረ መንግስት ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ይህንን ለመወጣት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃንም በአጭር ጊዜ ህዝቡ ጋር ተደራሽ የመሆን አቅማቸውን ለሀገረ መንግስት ግንባታ እንዲያውሉት ጠይቀዋል።
በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን በትውልድ ስብዕና ግንባታ ላይ በመስራት ለጠንካራ አገረ መንግስት ግንባታ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ፤ የወል እውነትና ዐቢይ ትርክት ላይ በማተኮር ለሁሉም ዜጎች የምትመች ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት ይገባል ብለዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉን ሊያስተሳስሩ በሚችሉ እሴቶች ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ "የሀገራዊ ማንነት እና ሀገራዊ እሴቶች" በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና የብዝሃነት ተመራማሪ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ፤ ሀገራዊ ማንነት የአንድ አገር ህዝብ የሚታወቅበት የጋራ መገለጫ ነው ብለዋል፡፡
አገራዊ እሴቶች የራስን ትክክለኛ ማንነት ለማወቅ እንደሚጠቅሙ ገልጸው እነዚህን ለዜጎች እና ተቋማት አቅጣጫን የማመላከት አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ማንነት ከሌሎች የሚለይበት የራሱ ባህሪያት ያሉት መሆኑንም ገልጸዋል።
‘ሀገራዊ ጥቅሞች ለሀገር ግንባታ’ በሚል የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዳይሬክተር አስማ ረዲ፤ የጋራ ራዕይ በመሰነቅ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ የጋራ እሴቶችን መገንባት ይገባል ብለዋል።
የመገናኛ ብዙሃንም ህዝቡን አንድ ሊያደርጉ በሚችሉ ትርክቶች ላይ ይበልጥ ትኩረት አድረገው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡