ቀጥታ፡

በመዲናዋ የአረጋውያንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ -የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ)፡-በመዲናዋ የአረጋውያንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዓለም አቀፉን የአረጋዊያን ቀን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት በሜቄዶንያ የአረጋውያን ማእከል አክብሯል።

በእለቱም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የመቄዶንያ የአረጋዊያን ማዕከልን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡


 

ቀኑም "የአረጋውያንን መብት ማክበር ትውልድን ለማሻገር" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

እንዲሁም የአረጋውያንን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመፍታት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋጥጥ በሚያስችሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይንሸት ዘሪሁን ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ፀንታ እንድትቆም በየዘመናቱ የነበሩ ትውልዶች የማይተካ ሚና ተጫውተዋል ነው ያሉት፡፡

የቀደመው ትውልድ ቅኝ ግዛት ያልተያዘች ለመላው አፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ሀገርን ለትውልዱ ጠብቀው አስረክበዋል ብለዋል፡፡

እንዲሁም የኢትዮጵያውያን አብሮ የመኖር እሴቶች ጠብቀው እንዲቆዩ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የአረጋውያንን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አጋር አካላትን ያሰተፈ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ለአብነትም በከተማዋ 30 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የአረጋውያንን ማእከልን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ገንብቶ ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጸዋል፡፡

በማእከሉም ከ700 በላይ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ አረጋውያንን ተቀብሎ በማገዝ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ጌታቸው ክፍሉ በበኩላቸው ትውልዱ የበጎነትና እርስ በርስ የመረዳዳት እሴቶችን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ አለበት ብለዋል፡፡

አገርን መውደድ እና ጠንካራ የስራ ባህልን በማጎልበት ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ከፍታዋ መመለስ እንደሚገባም እንዲሁ፡፡

የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መስራችና ስራ አስኪያጅ   ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው፤ኢትዮጵያን ያገለገሉ ባለውለታ አረጋውያንን ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል። 

መንግስት፣ተቋማትና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለማዕከሉ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የአረጋውያን ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ 33ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ 32ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም