ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያን በበጎ ገጽታ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ምንጭ እንዲሆን እየሰራን ነው - የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያን በበጎ ገጽታ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ምንጭ እንዲሆን እየሰራን ነው - የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ

አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ)፦ ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያን በበጎ ገጽታ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ምንጭ እንዲሆን እየሰራን ነው ሲሉ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ገለፁ፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ1993 ዓ.ም የተጀመረና በየዓመቱ የሚከናወን የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ነው።
በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችን በማፍራት የራሱን ድርሻ ማበርከቱም ይታወቃል።
ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም ለ23 ተኛ ጊዜ በሚከናወነው በታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ ከ45 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ለአሸናፊነት እንደሚፎካከሩበት ተጠቁሟል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ "ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ" ኢትዮጵያን በጎ ገጽታ እንዲያስተዋወቅና የቱሪዝም ምንጭ እንዲሆን እየሰራን ነው ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።
መርኃ ግብሩ የስፖርት ዲፕሎማሲውን ከማጠናከር ባለፈ ኢትዮጵያዊ አብሮነትን በተግባር ለማሳየት የሚያግዝ ትልቅ ውድድር እንደሆነም ጠቁመዋል ።
ውድድሩን የተሻለ ለማድረግ ያለፉ መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀምና ልምድ በመውሰድ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአካባቢ ፅዳት፣ በአረንጓዴ አሻራና መሰል ተግባራት ላይ በመሳተፍ አርአያ ለመሆን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
በዘንድሮው ውድድር በሁለቱም ፆታዎች አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች 200 ሺህ ብር ፣ሁለተኛ ለሚወጡ 100 ሺህ፤ ሦስተኛ ለሚወጡት ደግሞ የ50 ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
ከ 4ተኛ እስከ 8ተኛ ለሚወጡ አትሌቶች ሽልማት እንደተዘጋጀላቸው በመጠቆም በውድድሩ ሪከርድ ለሚያሻሽሉ አትሌቶች የ50 ሺህ ብር ተጨማሪ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ገልጸዋል።
በውድድሩም 20 አምባሳደሮችና የ37 ኤምባሲ ተወካዮች እንደሚሳተፉም ነው የተገለፀው።
ውድድሩን አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት፣ በሪሁ አረጋዊና አቤ ጋሻው ሶስት ሶስት ጊዜ ያሸነፉ ሲሆን በሴቶች ያለምዘርፍ የኋላው ሁለት ጊዜ አሸንፋለች።
በመጀመሪያው የታላቁ ሩጫ ውድድር ኃይሌ ገብረሥላሴ በወንዶች እና ብርሃኔ አደሬ በሴቶች አሸናፊ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ባለፈው ዓመት በተከናወነው የ22 ኛው ዙር የታላቁ ሩጫ ውድድር በወንዶች አቤ ጋሻው በሴቶች ደግሞ ትግስት ከተማ ማሸነፋቸው አይዘነጋም።
በዘንድሮው ውድድር የሚካፈሉ ታዋቂ አትሌቶች ስም ዝርዝር ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ እንደሚደረግም ተገልጿል።
የዘንድሮውን ውድድር በክብር እንግድነት የምታስጀምረው በባርሴሎና ኦሎምፒክ አትሌት ደራርቱ ቱሉን በመከተል በ10 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ያመጣችው ደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ኤላና ሜሪ እንደሆነች ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።