የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 29/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።
የዓለም የጥራት ቀን በኢትዮጵያ ለ12ኛ በዓለም ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ “ጥራት ለተሻለ የመወዳደር አቅም” በሚል መሪ ሃሳብ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ህዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
በአዲስ አበባ ቀኑን በማስመልከት አምራቾች የምርት ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ የሚያስችል ኤግዚቢሽን፣ አውደ ጥናትና የፍተሻ ላብራቶሪ ጉብኝት ተካሄዷል፡፡
በዚሁ ሁነት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ ምርትና አገልግሎቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል።
ለዚህም ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የ13 ሕንፃዎች ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፍተሻ መሣሪያም ተገዝቶ አገልገሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ፤ በተስማሚነት ምዘና አገልግሎት ዘርፍ የተሟላና ሁሉን አቀፍ አገልግሎት በአንድ ማዕከል እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአምራቾችና ለአገልግሎት ሰጪዎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና ዕውቅና ያለው አገልግሎት ለመስጠት ድርጅቱ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም ገልጸዋል።
የፍተሻ ላብራቶሪ፣ የኢንስፔክሽንና የሰርቲፊኬሽን አገልግሎት አምራቾች በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲታወቁና ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ምርት ለሸማቹ እንዲያቀርቡ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።