የትራንስፖርት አገልግሎት ማሻሻያ ካውንስል መቋቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ችግሮች እንዲሻሻሉ ትልቅ አቅም የፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የትራንስፖርት አገልግሎት ማሻሻያ ካውንስል መቋቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ችግሮች እንዲሻሻሉ ትልቅ አቅም የፈጠረ ነው
አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ)፦ የትራንስፖርት አገልግሎት ማሻሻያ ካውንስል መቋቋሙ በዘርፉ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ችግሮች እንዲሻሻሉ ትልቅ አቅም የፈጠረ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።
ሚኒስቴሩ የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸሙን ለትራንስፖርት አገልግሎት ማሻሻያ ካውንስል አቅርቧል።
በመድረኩ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ፤ ሚኒስትር ዴኤታዎች፤የካውንስሉ ሰብሳቢ ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።
ዶክተር አለሙእንዳሉት በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲያግዝ የተቋቋመው የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ካውንስል አገልግሎቶች እንዲሻሻሉ ትልቅ አቅም የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም፤ የትራንስፖርት ዘርፍ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የደም ስር መሆኑና የሀገሪቱ ገቢና ወጪ ዕቃዎች እያደገ ስለሆነ ዘርፉን ለማሻሻል እና ለማዘመን የሁሉም የባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህም በተለይ የትራንስፖርት አገልግሎት ማሻሻያ ካውንስል ለሚያደርገው ጥረት አመስግነዋል::
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ የማድረግ፤ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ የማሻሻል ላይ አበረታች ስራዎች መስራቱ ተገልጿል።
በተጨማሪም፤ በህዝብና ጭነት ትራንስፖርት አገልግሎቶችን የማሻሻል፤ በአቪዬሽን ዘርፍ፤ በባቡርና ትራንስፖርት አገልግሎት፤ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ላይ ባለፉት ሶስት ወራት አበረታች ስራዎች መሰራታቸው ተገልጿል።
የትራንስፖርት አገልግሎት ማሻሻያ ካውንስል ፕሮጀክት ማናጀር ሳምራዊት አምደወርቅ ካውንስሉ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ በመናኸሪያዎች አገልግሎት አሰጣጥ ምልከታን፤ በፐብሊክ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ የተገልጋዩን ህብረተሰብ አስተያየቶች ያሉበትን ደረጃ በዝርዝር አቅርበዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር አገልግሎት አሰጣጥ፤ የኢትዮጵያ ሲቪል በአቪዬሽን ባለስልጣን ላይ ካውንስሉ ያደረገውን የክትትል እና ድጋፍ እንዲሁም የተገልጋዩ ህብረተሰብ አስተያየቶች ያሉበትን ደረጃ በዝርዝር አቅርበዋል::
በመድረኩ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ከተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ እና ማብራሪያ መስጠታቸውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።