የህብረት ስራ ዘርፍ ሪፎርም የተፈለገውን ለውጥና ውጤት እንዲያመጣ የዘርፉ ኃላፊዎች ርብርብ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የህብረት ስራ ዘርፍ ሪፎርም የተፈለገውን ለውጥና ውጤት እንዲያመጣ የዘርፉ ኃላፊዎች ርብርብ ያስፈልጋል

አዳማ ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ)፡-በሀገር ደረጃ የተጀመረው የህብረት ስራ ማህበራት ልማትና ዕድገት ሪፎርም የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ በየደረጃው ያሉ የክልሎች የዘርፉ አመራሮች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስገነዘበ።
የሁሉም ክልሎች የህብረት ስራ ዘርፍ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉበትና በዘርፉ በተጀመረው ሪፎርም ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝና ለተፈፃሚነቱ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ውይይት ዛሬ በአዳማ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ የህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙን በማሳካት ረገድ የህብረት ስራ ማህበራት ሚና የጎላ ነው።
ለዚህም የአርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩንና የከተማ ነዋሪዎች የቁጠባ አቅም ከማጎልበት አኳያ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ የህብረት ስራ ማህበራትን ጨምሮ የገበሬዎችንና የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በተለይም የህዝቡ የቁጠባ ባህል በማጎልበትና የፋይናንስ አቅም በመፍጠር ዩኒየኖችና መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት የራሳቸውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት መፍታት እንዲችሉ ሪፎርሙ አስፈልጓል ብለዋል።
ዘላቂ የፋይናንስ አቅርቦቱን ሊያሳኩ ከሚችሉ ጉዳዮች ዋነኞቹ ደግሞ ሀገር አቀፍ የህብረት ስራ ባንክ፣ የህብረት ስራ ፈንድና ኢንሹራንስ ማቋቋም መሆኑን አንስተዋል።
ሪፎርሙ የህብረት ስራ ዩኒየኖች የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ የሜከናይዜሽን መሳሪያዎችና የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር በራሳቸው ከውጭ እንዲያስገቡ የሚያስችል አቅም በሂደት ለመፍጠር ግብ መያዙንም ጠቅሰዋል።
ሪፎርሙ ተግባራዊ የሚሆነው ከፌዴራል እስከ ክልል ባሉ የህብረት ስራ ሴክተሮች፣ ዩኒየኖችና መሰረታዊ ማህበራት ውስጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህን ሁሉ የሚያመቻች የህብረት ስራ ሊግ ይመሰረታል ብለዋል።
በዚህም የሪፎርሙ አተገባበር ሂደት ወጥነት እንዲኖረውና የተፈለገው ለውጥና ውጤት እንዲመጣ ከክልሎች የዘርፉ አመራሮች ጋር የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ለተፈፃሚነቱ በትብብር ለመስራት መድረኩ አስፈልጓል ብለዋል።
ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረውን ንቅናቄ በማስተባበርና በመምራት ረገድ የክልሎች የህብረት ስራ ዘርፎች በባለቤትነት መንፈስ በጋራ መስራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የአማራ ክልል የህብረት ስራ ማህበራት ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ጌትነት አማረ እንዳሉት ሪፎርሙ የማህበራትን የፋይናንስና የካፒታል አቅም ለማጠናከር የጎላ ሚና ያለው የለውጥ መሳሪያ ነው።
በተለይም በመሰረታዊ ማህበራትና ዩኒየኖች ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በመፍታትና ኋላ ቀር አሰራሮችን የሚያስወግድ ከመሆኑም ባለፈ የገበያ ተወዳዳሪነታቸውን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት "አብዛኞቹ የክልሉ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በስም ብቻ ያሉና ከደረጃ በታች ናቸው" ያሉት አቶ ጌትነት፤ በክልሉ ሪፎርሙን ያማከለ የዩኒየኖች ምዘናና ደረጃ ማውጣት ስራ ይከናወናል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረት ስራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ተገኝ በበኩላቸው ማህበራቱ ከአደረጃጀት ጀምሮ ያለባቸውን የወጥነት፣ የብልሹ አሰራር፣ የአመሰራረትና አስተዳደር ዘይቤያቸውን የሚቀይር ሪፎርም መሆኑን ተናግረዋል።
የማህበራቱና ዩኒየኖች የቦርድ አመራሮች ከአርሶ አደሩ የተወከሉ በመሆናቸው በዩኒየኖች ስራ አስኪያጅ የግል ፍላጎት ላይ ተመሰርተው የሚንቀሳቀሱትን መቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ሪፎርሙን ለማሳካትም በቀጣይ ከክልል ጀምሮ እስከ መሰረታዊ ማህበራትና ህብረተሰቡ ድረስ ንቅናቄና ግንዛቤ በመፍጠር ለውጤታማነቱ የሚናችንን እንወጣለን ሲሉም ተናግረዋል።