ቀጥታ፡

ሀገራዊ ጥቅሞች ላይ በጋራ መስራት ለሀገራዊ ብልጽግናና ህልውና መጠበቅ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ) ፦ ሀገራዊ ጥቅሞች ላይ በጋራ መስራት ለሀገራዊ ብልጽግናና ህልውና መጠበቅ ወሳኝ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዳይሬክተር አስማ ረዲ ገለጹ።

“የሀገር ግንባታ መሠረታውያን” በሚል መሪ ሀሳብ በሰላም ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዳይሬክተር አስማ ረዲ ‘ሀገራዊ ጥቅሞች ለሀገር ግንባታ’ በሚል ሀሳብ ላይ መወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በዚህም ሀገራዊ ጥቅም ሲባል ማንኛውም ዜጋ ሊያውቀው የሚገባና ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሀገራዊ ጥቅሞች ላይ በጋራ መስራት ለሀገራዊ ብልጽግናና ህልውና መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው የምንሰራቸው ስራዎች ሁሉ ለሀገራችን ጥቅም እና ዘላቂነት የሚፈይዱ መሆን እንዳለባቸው አንስተዋል።

ሁሉም ዜጋ የተግባባበት ሀገራዊ ጉዳይ ሲኖር የጋራ ራዕይ መፍጠርና ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻልም ገልጸዋል።

ሀገራዊ ጥቅሞችን ማስረፅ ከቤተሰብ ሊጀምር እንደሚገባ ዳይሬክተሯ ጠቁመው ትምህርት ቤቶች እና የሚዲያ ተቋማትም በዚህ ዙሪያ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም