ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ ዜጎች ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ ዜጎች ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል
አዲሰ አበባ ፤ ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ) ፦ ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ ዜጎች ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለምክክሩ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት፡፡
አፈ ጉባኤው ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአራት ወራት አፈጻጸሙ ለምክር ቤቱ ቀርቦ በተገመገመበት ወቅት ነው።
ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ቀሪ የዝግጅት ስራዎችም አካታችነት እያረጋገጡ መሄድ ተገቢ ነው ብለዋል።
ለዚህም በየደረጃው ያሉ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎችን ማሳተፍ፣ አጀንዳዎቻቸውን በአግባቡ መሰብሰብና የሁሉም ህዝብ ሀሳቦች የሚደመጡበት መድረክ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ኮሚሽኑ በህግ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በአግባቡ እየተወጣ መሆኑ በተጨባጭ እየታየ ነው ያሉት አፈ-ጉባኤው፤ ለስራዎቹ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት ምክር ቤቱ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር የሚካሄደው ምክክር አሳታፊ፣ ግልፅና አካታች በሆነ መንገድ እንዲሆን የምክር ቤት አባላት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሁነኛ መፍትሄ በመሆኑ ዜጎች ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው ጥሪ ያቀረቡት።