የወል እውነትና ዐቢይ ትርክት ላይ በማተኮር ለሁሉም ዜጎች የምትመች ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት አለብን - አቶ ታዬ ደንደአ - ኢዜአ አማርኛ
የወል እውነትና ዐቢይ ትርክት ላይ በማተኮር ለሁሉም ዜጎች የምትመች ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት አለብን - አቶ ታዬ ደንደአ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ) ፦ የወል እውነትና ዐቢይ ትርክት ላይ በማተኮር ለሁሉም ዜጎች የምትመች ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት አለብን ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ተናገሩ።
“የሀገር ግንባታ መሠረታውያን” በሚል መሪ ሀሳብ የሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋራ ያዘጋጁት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ "የሀገር ግንባታ መሠረታውያን መነሻ ጉዳዮች" በሚል ርዕሰ ጽሁፍ ያቀረቡት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ሀገረ መንግስት የሁሉም መሰረታዊ ጥቅሞች ማዕከል ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የሀገር ግንባታ የህዝቡን ትስስርና የጋራ ራዕይ ማጠናከር መሆኑን ገልጸው ሀገርን ለመገንባት በቁልፍ የወል ጉዳዮች ላይ መግባባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመሆኑም ለሀገር ግንባታ የጋራ ግቦችና ትውስታዎች፣ የጋራ ታሪክና የወል ጥቅሞች፣ የጋራ ስኬቶች፣ ስጋቶችና ሌሎች ግብዓቶችን በመለየት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የወል እውነትና ዐቢይ ትርክት ላይ በማተኮር ለሁሉም ዜጎች የምትመች ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና የብዝሃነት ተመራማሪ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ፤ "የሀገራዊ ማንነት እና ሀገራዊ እሴቶች" በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
ሀገራዊ ማንነት የአንድ አገር ህዝብ የሚታወቅበት የጋራ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያውያን ማንነት ከሌሎች የሚለይበት የራሱ ባህሪያት አሉት ብለዋል።
ከኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫዎች መካከል ብዝሃ ቋንቋ፣ ጀግንነት፣ ቀደምትነት፣ የባህል ሃብቶችና ግብረ ገባዊነት ከብዙዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
በመሆኑም እነዚህንና ሌሎችንም እምቅ ሀገራዊ እሴቶች በማጉላት የራስን ትክክለኛ ማንነት ማጎልበትና መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።