የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ54 ሚሊዮን በላይ ደርሷል- የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ54 ሚሊዮን በላይ ደርሷል- የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ) ፦የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ54 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና ውይይት እየተካሄደ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በጤናው ዘርፍ ውጤታማ የለውጥ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የጤና ተደራሽነትና ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡
አካታችና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳካት ከተቀረጹ ሪፎርሞች መካከል አንዱ የጤና መድህን ስርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
የጤና መድህን ስርዓት በጤናው ሴክተር ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያስገኘ መሆኑንም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ወርቁ በበኩላቸው የጤና መድህን ስርዓት ዓላማ ዜጎች አስቀድመው በሚከፍሉት መዋጮ የጤና እክል በሚያጋጥማቸው ወቅት ያለምንም የክፍያ ስጋት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል ነው።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ54 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም ተናግረዋል፡
ከዚህም ውስጥ 10 ሚሊዮን የሚሆኑት የመክፈል አቅም የሌላቸውና ዓመታዊ መዋጯቸው በመንግስት የተሸፈነላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ስርዓቱ እንዲጠናከር የመምራትና የመደገፍ ሂደት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡