ቀጥታ፡

በ1 ሺህ 400 ወረዳዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ እየተሰራ ነው --ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያ በ1 ሺህ 400 ወረዳዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ  እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እያካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የ4 ወራት የስራ አፈጻጸም ሂደት፣ የተገኙ ስኬቶችና የገጠሙ ችግሮች ላይ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ በዝግጅት ምዕራፍ የተሳታፊዎች ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በተለያዩ ክልሎች በመካሄድ ላይ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ ከህዝቡ በምክክሩ የሚሳተፉ አካላትን ልየታን ከታች ከቀበሌና ከጎጥ ጀምሮ በአካታችና በተዓማኒነት እየከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡


 

ለዚህ ስኬት የሃይማኖት አባቶች፣ እድሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መምህራን ማህበር፣ የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ዘጠኝ የማህብረሰብ ክፍሎች ተለይተው እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስካሁኑ የልየታ ሂደት በተለያየ ምክንያት ከቀድሞ መኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማካተት ስራ መከናወኑንም  ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰር መሰፍን አርዓያ አክለውም በሀገራዊ ምክክሩ በሀገሪቱ 1 ሺህ 400 ወረዳዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተወካዮቻቸው አማካይነት በተገቢው ሁኔታ እንዲሳተፉ ይደረጋል ነው ያሉት።

የሀገራዊ ምክክር ሂደትን እሳቤንና በተመለከተ በተለያዩ ቋንቋዎች ለህብረተሰቡ የማስገንዘብ ተግባራትም ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም