ለሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት መሳካት የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት መሳካት የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ) ፦ ለኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት መሳካት የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ።
"የሀገር ግንባታ መሠረታዊያን " በሚል መሪ ሃሳብ የሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋራ ያዘጋጁት የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፤ የሀገረ መንግስት ግንባታ የሁሉም ዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎና እገዛ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የአገረ መንግስት ግንባታ ስራ በአንድ ጊዜ የሚያልቅ ባለመሆኑ ለሀገራዊ አንድነት መጠናከር የሁላችንም አደራ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የአገረ መንግስት ግንባታን ለማሳካት የጋራ ማንነትን መገንባት፣ ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ እና ብሔራዊ እሴቶች ላይ ማተኮር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
በሀገረ መንግስት ግንባታ ብዝሃነትን በአግባቡ አለማስተናገድ እንደተግዳሮት የሚጠቀስ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
በመጠፋፋት ላይ ተመስርቶ ለዘመናት የዘለቀውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል በመቀየር ሁሉንም የሚያሳትፍ የዴሞክራሲያዊ ባህልን መገንባት ይገባል ብለዋል።
በዚህ ሂደት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሁሉም ዜጋ ተሳትፎና ርብርብ የሚያስፈልግ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤን ጨምሮ ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የሀገር ግንባታ መሠረታዊያን መነሻ ጉዳዮች፣ ሀገራዊ ማንነትና እሴቶች ለሀገር ግንባታ፣ ሀገራዊ ጥቅሞችና ሌሎችንም ሀገራዊ ጉዳዮች የሚዳስሱ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት እየተደረገ ይገኛል።