የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ አዲስ ለሚገነባው ብሄራዊ የአረጋውያን ማዕከል ግንባታ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች - ኢዜአ አማርኛ
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ አዲስ ለሚገነባው ብሄራዊ የአረጋውያን ማዕከል ግንባታ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 29/2016 (ኢዜአ) ፦ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በኢትዮጵያ አዲስ ለሚገነባው ብሄራዊ የአረጋውያን ማዕከል ግንባታ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ አምባሳደር ሙሐመድ ሳሬም አልረሺዲ ጋር ተወያይተዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ለአረጋውያን የህክምና፣ የገቢ ማስገኛ እና ሁለገብ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል ማዕከል ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ለአምባሳደሩ አብራርተዋል።
ደረጃውን የጠበቀ የአረጋውያን ማዕከል ለመገንባት የዲዛይን ስራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ያሉት ሚኒስትሯ ለግንባታው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ አምባሳደር ሙሐመድ ሳሬም አልረሺዲ የኢትዮጵያ መንግስት በብሔራዊ ደረጃ ለሚያስገነባው የአረጋውያን ማዕከል ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።
አክለውም፤ ሚኒስቴሩ አረጋውያንን ጨምሮ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ህይወት ለመለወጥ እና ለማሻሻል እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የሀገር ባለውለታ የሆኑት አረጋውያንን መብት ለማስከበር፣ ማህበራዊ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅና የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የሚረዳ ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂ በመንደፍ በስራ ላይ ማዋሉን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።