በጌዴኦ ታሪካዊ መካነ ቅርስ ላይ ጥናት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጌዴኦ ታሪካዊ መካነ ቅርስ ላይ ጥናት እየተካሄደ ነው
ዲላ ፤ ጥቅምት 28 / 2016 (ኢዜአ):- የጌዴኦ ታሪካዊ የትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።
በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የስነ ቅርስ ጥናት ባለሙያ አቶ ትኩዬ አርብሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ ቅርሶችን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ /ከማስመዝገብ ባለፈ የልየታና ጥበቃ ተግባራት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ ነው።
ከስራውም ውስጥ የጌዴኦ ታሪካዊ የትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ እየተካሄደ ያለው ጥናት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጥናቱም የቁፋሮ፣ የትክል ድንጋዮች ቆጠራና ይዘት ልየታን ከማካተት ባለፈ ቅርሱ ያለበትን ደረጃና ተጨማሪ ታሪካዊ ዳራ የሚቃኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር በዩኔስኮ መመዝገቡ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ መስህቡ ያለበትን ደረጃ መለየትና መከባከብ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በተለይ የመዳረሻዎች ልማት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአካባቢው ማህበረሰብ ቅርሱን በዘላቂነት እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ የባለቤትነት ስሜት ማስረጽ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር አራት ታሪካዊ መካነ ቅርስ ትክል ድንጋዮችን ጨምሮ የተለያዩ ጥብቅ ደንና ተፈጥሯው መስህቦችን ያቀፈ መሆኑን ያስረዱት ደግሞ የጌዴኦ ባህልና ቅርስ ተመራማሪ እጩ ዶክተር ፀጋዬ ታደሰ ናቸው።
በተለይ አለም አቀፍ ሁለተናዊ የሰው ልጆች እሴት ሆኖ የተመዘገበው የአካባቢ ጥበቃ ባህሉ ከቅርስ ባለፈ የግብርናና የህዝቡ የአኗኗር ስርዓት መሰረት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በታሪካዊ የትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ ላይ ከ20 ዓመታት በፊት ከፈረንሳይ በመጡ የስነ ቅርስ ጥናት ባለሙያዎች የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን እየተካሄደ ያለው ጥናት ለተጨማሪ ግኝትና ቅርሱ ያለበትን ደረጃ ለመለየት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ በዘርፉ መረጃ የሚፈልጉ ጉብኝዎችና አጥኚዎች አሁናዊ የተሻሻለ መረጃ በመስጠት የጥናቱን ውጤት መሰረት ያደረገ የእንክብካቤና ጥበቃ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በጌደኦ ከ6 ሺህ በላይ ትክል ድንጋዮች እንደሚገኙ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ያለውና የመካነ ቅርሱ አካል የሆነው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ ዕውቅና በማግኘት መመዘገቡ ይታወሳል።