ኢትዮጵያ የ "ታላቁ አረንጓዴ ግንብ ኢኒሼቲቭ" ብሔራዊ ጥምረት በይፋ አቋቋመች

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 28/2016 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ የታላቁ አረንጓዴ ግንብ ኢኒሼቲቭን በተቀናጀ አግባብ መምራት የሚያስችላትን ብሔራዊ ጥምረት ዛሬ በይፋ አቋቋመች፡፡

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2007 ይፋ የሆነው ታላቁ አረንጓዴ ግንብ ኢኒሼቲቭ፤ በረሀማነትን ለመከላከል 8 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ደን በሳሄል ቀጣና ለመትከል ያለመ ግዙፍ አህጉራዊ ፕሮጀክት ነው። 


 

የኢንሼቲቩን አስመልክቶ የተዘጋጀ ውይይት ዛሬ በአፍሪካ ሕብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄዷል።

ኢትዮጵያም ኢንሼቲቩን ከመሰረቱና ስምምነቱን ከፈረሙ 11 የአፍሪካ አገራት አንዷ ስትሆን፤ በዛሬው መድረክም ኢኒሼቲቩን በተቀናጀ አግባብ መምራት የሚያስችላትን ብሔራዊ ጥምረት አቋቁማለች።

ጥምረቱ የፌደራልና የክልል መንግስታት እንዲሁም ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የልማት አጋሮችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ነው፡፡

በዚህም ጥምረቱ ትግበራውን ወጥ የማድረግና ለዚህም የሚያስፈልገውን ሀብት በተቀናጀ መልኩ የማሰባሰብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሞቱማ ቶሌራ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቩን በአማራ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች በሚገኙ 58 ወረዳዎች እየተገበረች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ትግበራው በተለያዩ ምክንያቶች በወረዳዎቹ የተራቆተውን 13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ዳግም በደን የመሸፈን ዓላማ እንዳለው አመልክተዋል።

መርሐ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለደን ልማት ስራዎች ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢኒሺዬቲቩ ኢትዮጵያ በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ እየተገበረቻቸው ላሉ የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፎች ትግበራ አበርክቶ እንደሚኖረውም ነው ዶክተር ሞቱማ ያስረዱት።

ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

ከዚህም አንጻር ኢኒሼቲቩ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ጋር የሚተሳሰር እንደሆነ በማንሳት።

በመሆኑም ዓለም አቀፍ አጋሮች ለትግበራው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።


 

በአፍሪካ ሕብረት የ"ታላቁ የአፍሪካ አረንጓዴ ግንብ ኢንሼቲቭ" አስተባባሪ ዶክተር ኤልቪስ ፖል ኢኒሼቲቩ አህጉሪቷ በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የፓን አፍሪካ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የተራቆተ መሬትን መልሶ በደን መሸፈን እያከናወነች ያለችው ተግባር ለሌሎች አፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።

በመሆኑም አህጉራዊው ተቋም ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።


 

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በረሃማነትን የመከላከል ማዕቀፍ(UNCCD) የ"ታላቁ የአፍሪካ አረንጓዴ ግንብ ኢንሼቲቭ" ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ቢርጊ ላሚዛና በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለኢኒሼቲቩ ትግበራ የሚያስፈልገውን ብሔራዊ ጥምረት ያቋቋመች 10ኛዋ አፍሪካዊት አገር መሆኗን ጠቁመዋል።

ጥምረቱ ለኢኒሼቲቩ ትግበራ የጋራ አቅም ከማሰባሰብና ትብብር ከመፍጠር አኳያ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ አጋሮችም ለመርሐ ግብሩ ትግበራ የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የደን ልማት "የታላቁ አረንጓዴ ግንብ ኢኒሼቲቭ" አፈጻጸምና የብሔራዊ ጥምረቱን አስመልክቶ የመነሻ ጽሁፍ  አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ብሔራዊ ጥምረቱ የዝግጅት ስራዎቹን አጠናቆ በቀጣይ ሳምንታት ወደ ስራ እንደሚገባ በመድረኩ ላይ ተገልጿል። 

በስብስባው የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሞቱማ ቶሌራ፣ የአፍሪካ ሕብረት ግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽን ተወካዮች ፣የደን  ልማት፣ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ላይ የሚሰሩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።  

የ"ታላቁ አረንጓዴ ግንብ ኢኒሼቲቭ" ኢትዮጵያን ጨምሮ በ22 የአፍሪካ አገራት እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን በአህጉሪቷ የተራቆተ 100 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መልሶ በደን የመሸፈን ግብ ያለው ፕሮጀክት ነው። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም