ቀጥታ፡

በሰቆጣ ከተማ ድጋፍ ለሚሹ ለ400 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶች ተበረከተ

ሰቆጣ፤  ጥቅምት 28 /2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማትና የክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በሰቆጣ ከተማ ድጋፍ ለሚሹ ለ400 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶችን አበረከተ።

በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ላይ በኮሚሽኑ የዋግ ኽምራ ሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ሃይለማርያም መልካሙ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ  ወገኖች እያገዘ ነው።

ባለፈው  ወር ቤተሰቦቻቸው የገንዝብ እጥረት ላለባቸው 400 ተማሪዎች የደብተርና እስክብሪቶ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

ዛሬ ደግሞ ለእነዚሁ ተማሪዎች 500 ሺህ ብር ግምት ያለው የደንብ ልብስ ድጋፍ አድርጓል።

ኮሚሽኑ በተጨማሪ  200 አጋዥ መፅሃፍትን በሚቀጥለው ሳምንት ለተማሪዎቹ ድጋፍ እንደሚያደርግም ባለሙያው አስታውቀዋል።

በዘንድሮው ትምህርት ዘመን ኮሚሽኑ በሰቆጣ ከተማ ድጋፍ ለሚሹ  ተማሪዎች በአጠቃላይ ያደረገው ድጋፍ 950 ሺህ ብር ግምት ያለው የትምህርት ቁሳቁስ መሆኑን አመልክተዋል።

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ታምሩ ካሳሁን በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ  ለሚገኙ ቤተሰብ ተማሪዎች የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን አረጋግጠዋል።

ድጋፉም የተማሪዎች የደንብ ልብስን  ደብተር፣ እስክብሪቶና እርሳስን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድጋፉም የተማሪዎቹን  ችግር ያቃለለ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ለልጆቻቸው ያደረገው የደንብ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ የነበረባቸውን ችግር እንዳቃለለላቸው የገለጹት ደግሞ የተማሪ ወላጅ  አቶ በሪሁን አሻግሬ ናቸው።

ድጋፉ  በመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ የረዳ መሆኑን  የኮሎኔል አማረ ሞላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ግርማ ማሞ ተናግረዋል።

የኮሎኔል አማረ ሞላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ አብይ ጎበዜ በበኩሉ፤የተደረገለት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በተሟላ መንገድ ትምህርቱን ለመማር እንደሚያስችለው ተናግሯል።

ኮሚሽኑ ካደረገው የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ በተጨማሪ ለከተማ አስተዳደሩ ሴቶች ማህበር የተለያዩ የቢሮ ውስጥ መጠቀሚያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም