ኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወትን በመጠበቅ ረገድ አብነት የሚሆን ተግባር እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 28/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወትን በመጠበቅ ረገድ አብነት የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኑ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ማዕከልና ኔትዎርክ ድርጅት የብዝሃ-ህይወት ጥበቃን የተመለከተ የመጀመሪያው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው፡፡  

  የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶችን ማቅረብ  ሲሆን፤ ከበርካታ የአፍሪካ አገራት የመጡ  ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ቀንድ የአካባቢ ማዕከልና ኔትዎርክ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር መኩሪያ አርጋው፤ በአውደ ጥናቱ የአገራት ልምድና ተሞክሮ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል፡፡

ይህም አገራት ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሰቦችን እንዲወስዱ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡  


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብትና ብዝሃ ህይወትን ለመጠበቅ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ የአረንጓዴ አሻራ እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ  ስራዎችን አንስተዋል፡፡

በዚህም አከባቢና ብዝሃ ህይወትን ከመጠበቅ ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

   በአውደ ጥናቱም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በብዝሃ ህይወት ጥበቃ እና በሌሎችም ዘርፎች ያከናወነቻቸውን ስራዎች በተሞክሮነት እንደምታቀርብም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በብዝሃ ህይወት ጥበቃ እያከናወነች ያለውን ተግባርም ከአምስት የአፍሪካ አገራት ለተወጣጡ ልዑካን ቡድኖች ልምድ ማካፈሏን ጠቁመዋል፡፡

   ኢትዮጵያ የአፍሪካን አንድ ሶስተኛ የሚሆን ብዝሃ-ህይወት ክምችት አላት ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማሪዮ ናቸው፡፡


 

ለአብነትም ከ90 ሺህ በላይ የብዝሃ ህይወት ናሙናዎች ተጠብቀው እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡     

እነዚህም የአየር ንብረት ለውጡን ተቋቁመው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለሚሆኑ የምርመር ስራዎች ፋይዳቸው የጎላ መሆኑንም  ገልጸዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይወት እና የስነ-ምህዳር አገልግሎቶች ተቋም አስተባባሪ ዶክተር ሄኒንግ ሶመር፤ ተቋሙ  አገራት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የብዝሃ ህይወት እና ስነምህዳር ጠበቃ እንዲያከነወኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡  


 

በቀጣይም አገራት ለብዝሃ-ህይወት እና ስነ-ምህዳር አያያዝ ትኩረት በመስጠት የአየር ንብረት ለውጥን ሊከላከሉ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡     

አውደ ጥናቱ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የተለያዩ አገራት ተሞክሮን የያዙ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርቡም ተገልጿል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም