ኢትዮጵያ የግል ባለሃብቶች በታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚፈቅድ ህግ እያዘጋጀች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የግል ባለሃብቶች በታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚፈቅድ ህግ እያዘጋጀች ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 28/2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የግል ባለሃብቶች በታዳሽ ኃይል ማመንጨትና ማሰራጨት ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚፈቅድ የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሱልጣን ወሊ ገለጹ፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና አለም አቀፍ ሶላር አሊያንስ በኢትዮጵያ የጸሃይ ሃይል ልማትን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ምክክር ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂደዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሱልጣን ወሊ እንዳሉት፣ በ2022 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይልን ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡
በእቅዱ መሰረት 65 በመቶው የሚሆነው የኃይል ፍላጎት ከብሔራዊ ግሪድ የሚቀርብ ሲሆን ቀሪው 35 በመቶው ከዋና የኃይል ቋት ውጭ (ኦፍ ግሪድ) ይቀርባል ብለዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ከፀሐይ ብርሃን በአንድ ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ በሰዓት 5 ነጥብ 5 ኪሎ ዋት ኃይልን የማመንጨት አቅም ቢኖርም እስካሁን ጥቅም ላይ የዋለው ከ400 ሜጋ ዋት እንደማይበልጥ ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የግል አልሚዎች በዘርፉ ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩ አንደኛው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
ለአብነትም "አንድ የግል ባለሃብት በዘርፉ ተሰማርቶ ከጸሃይ ብርሃን ኃይል በማመንጨት መሸጥ ቢፈልግ ክፍያ የሚጠይቅበት የህግ ማዕቀፍ የለም" ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱም ሆነ ስርጭቱ በመንግስት ብቻ መከናወኑ ዕድገቱን አዝጋሚ አድርጎት መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ይህን አሰራር በመቀየር የግል ባለሃብቱ ወደ ዘርፉ እንዲገባ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች፣ አዋጆችና መመሪያዎችን ያጠቃለለ የህግ ማዕቀፍ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዛሬው ምክክር ለህግ ማዕቀፎች ዝግጅት ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የዓለም አቀፉ ሶላር አሊያንስ ተወካይ ፍሬህይወት ወልደሃና በበኩላቸው፣ ጥምረቱ በአባል አገራት የፀሐይ ኃይል ልማት እንዲስፋፋ የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጥምረቱን የተቀላቀለችው በፈረንጆች 2018 መሆኑን የገለጹት ተባባሪ ፕሮፌሰር ፍሬህይወት ወልደሃና ጥምረቱ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ነው የጠቀሱት፡፡
በተጨማሪም የግል ባለሃብቱ በስፋት ወደ ዘርፉ እንዲገባ ለማድረግ በተለያዩ ስፍራዎች ለማሳያ የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን እያከናወነና እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ ሶላር አሊያንስ የተመሰረተው በፈረንጆች 2015 ሲሆን የፀሐይ ብርሃን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል 116 ሀገራት የስምምነት ማዕቀፉን የፈረሙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ 94 ሀገራት ስምምነቱን ማጽደቃቸውን የጥምረቱ መረጃ ያሳያል።