የባህር በርን በተመለከተ በገንቢ ክርክር ወጣቱን በማሳወቅና የጋራ አቋም በመያዝ በትብብር ልንሰራ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በርን በተመለከተ በገንቢ ክርክር ወጣቱን በማሳወቅና የጋራ አቋም በመያዝ በትብብር ልንሰራ ይገባል
ሀዋሳ፤ጥቅምት 28 /2016 (ኢዜአ) ፦የባህር በር ባለቤትነትን በተመለከተ መላው ህዝብ፣ ምሁራንና ፖለቲከኞች በመነጋገርና በመከራከር ወጣቱን በማሳወቅና የጋራ አቋም በመያዝ በትብብር ልንሰራ ይገባል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ስለ "ከጠብታ ውሃ እስከ ባህር ውሃ" በሚል ርዕስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባለት ባደረጉት ገለፃ የባህር ጉዳይ ሁሉም በየደረጃው ሊወያይበት፣ የፖለቲካ ልሂቃን ሊነጋገሩበት የሚገባ መሆኑን መጥቀሳቸው ይታወሳል።
ይህን አስመልከተውም ጉዳዩ " ትልቅ ቁም ነገር ስለሆነ ቢያንስ እንወያይበት" ማለታቸውም እንዲሁ።
ምንም እንኳ ጉዳዩ ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ ያሉ ፖለቲካ ልሂቃን ፈራ ተባ እያሉ ቢያነሱትም በወቅቱ የነበረው መንግስት የባህር በር ጥያቄ እንዳይነሳ አጥብቆ ሲከለክል በመቆየቱ በጠረጴዛ ዙሪያ የሚቀርብ ሃሳብ አልነበረም።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና በሀዋሳ መምህራን ኮሌጅ ከ25 ዓመታት በላይ በዓለም አቀፍ የታሪክ መምህርነት ያገለገሉት አቶ አባቡ አሊጋዚ እንዳሉት፤ ከሁሉ በፊት መላው ህዝብ ምሁራንና ፖለቲከኞች በጉዳዩ ዙሪያ ተነጋግሮና ተከራክሮ አቋም ሊይዙ ይገባል።
''በመነጋገሩና በመከራከሩ ውስጥ የወጣቱን ግንዛቤ ማሳደግና ሚናው እንዲጎላ በትብብር መስራትም ይገባናል'' ብለዋል።
ለዚህም ከቤተሰብ እስከ ትምህርት ቤትና መምህራን እንዲሁም ከመንግስት ባለስልጣናት እስከ መገናኛ ብዙሃን ድረስ ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸው አውስተዋል።
ቀደምት የኢትዮጵያ ነገስታት ሲጠቀሙበት የነበረ ወደብ በታሪክ ስህተት አሁን ላለበት ሁኔታ መብቃቱ አሳዛኝ መሆኑን የገለፁት የታሪክ ምሁሩ፤ ጉዳዩ መነሳቱ ለዘመናት በውስጥ ሲድበሰበስ የቆየውን እውነታ ገሃድ እንዳወጣው አንስተዋል።
ለዘመናት በቀይ ባህር አካባቢ ሲፈጠሩ የቆዩ ችግሮች የትኛውም ዓይነት መልክና ባህሪ ቢኖራቸውም ኢትዮጵያ ያለባህር በር እንድታሳልፍ ያለማድረጋቸውን የሚናገሩት የታሪክ ምሁሩ አቶ አባቡ፤ በርበራና ዘይላን፣ አሰብና ምፅዋን ጨምሮ በሌሎች አማራጮች በቀጥታ ከዓለም አገሮች ጋር ስትገናኝ መኖሯን ታሪክ ምስክር ነው ብለዋል።
ታሪክም ይሁን ዓለም አቀፍ ህግ የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄን የሚፈቅድ መሆኑን ገልጸው፤ በታሪክ የተፈጠረውን ስህተት ለማከም መንግስት የጀመረውን በሰላማዊ መንገድ የማሳካቱ ጥረት ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የዓለም ዐቀፍ ሕግ መምህር የነበሩትና አሁን በሌላ የመንግስት ሥራ ሃላፊነት ላይ የሚገኙት አቶ ታደሠ አይበራ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን የመጠቀም ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መብቷን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ሀሳብ አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል።
ለዚህም መንግስት የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሠረት ያደረገ ውይይትና የዲፕሎማሲ ሥራ ላይ ማተኮር እንዳለበት አመላክተዋል።
ዓለም ዐቀፍ ሕጎችን ተከትሎ መግባባትን መፍጠርና በቀጣናው ሰላማዊ የሆነ የወንድማማችነት መንፈስ ያለው ጥያቄ በማቅረብ የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ላይ የጠለቀ ግንዛቤ ተፈጥሮ የጋራ እይታ እንዲሰፍን ማድረግ ሌላኛው በትኩረት መሰራት ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል።
ጉዳዩን ከወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳይ ጋር ከማገናኘት ይልቅ ከኢትዮጵያ የመልማት ፍላጎት አኳያ ብቻ ተመልክቶ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን መቆም እንደሚገባም አቶ ታደሰ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ መመለስ ዕድገቷ ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የሚያነሱት ደግሞ በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት መምህር አቶ ሙሉዓለም ኃይለ ማርያም ናቸው።
የኢትዮጵያ የወደብ በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሰጥቶ መቀበል መርህና ዲፕሎማሲን ማጠናከር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ሊደግፉን ከሚችሉ አገሮች ጋር አጋርነት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።