ቀጥታ፡

የስራ እድልና የክህሎት ልማት ተደራሽነትን የሚያሳልጡ መተግበሪያዎች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 28/2016 (ኢዜአ) ፦ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ እድል፣ የሙያ ብቃት ማረጋገጫና የኢንተርፕራይዝ አገልግሎት መስጫ መተግበሪያ ይፋ አደረገ።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፤ አዲስ ይፋ የሆኑት መተግበሪያዎች ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት የሚያግዙ መሆኑን ገልጸዋል።


 

አዲሱ መተግበሪያ የስራ ፈጠራን፣ የክህሎት ልማትንና የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በስራ እድል ፈጠራ ላይ የሚነሱ የፍትሐዊና ተደራሽነት ጥያቄዎችን ይፈታል ብለዋል።

የኢንተርፕራይዝ አገልግሎት መተግበሪያ የሆነውና ሉሲ የሚል ስያሜ የተሰጠው መተግበሪያ አንዱ ሲሆን ይህም የኢ-ኮሜርስ የንግድ ስረዓትን ለማስፋት ምቹ እድል የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።

ሌላው ብቁ በሚል የተሰየመው መተግበሪያም የስራ እድል ማግኛ፣ አሰሪና ሰራተኛን የሚያገናኝና ለሃሰተኛ መረጃ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል።

የሙያ ብቃት ማረጋገጥ (COC) የተሰኘው ሲስተምም እንዲሁ የምሩቃንን የሙያና ክህሎት ብቃት የመለካትና የማረጋገጥ ምዘናን ትክክለኛነት በማረጋገጥ በዘርፉ ብቁ ሙያተኛን ለማፍራትና ህገ-ወጥ አሰራርን ለማስቀረት ያስችላል ነው ያሉት።


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ የኢንተርፕራይዝ አገልግሎት መተግበሪያ ህገ-ወጥ የንግድ ስረዓቱን በማስቀረት የላቀ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ፍትሃዊና ጤናማ የንግድ ውድድር እንዲፈጠር በማድረግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው የተረጋጋና የተሳለጠ እንዲሆን የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ፤ ብቁ በሚል የተሰየመው መተግበሪያ ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ እድል ማግኛ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህም በአሰሪና ሰራተኛ በኩል የሚደርሰውን የትኛውንም አይነትኢ-ፍትሃዊ አሰራር በማስቀረት ፍትሃዊ የስራ ሁኔታን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።


 

የሙያ ብቃት ማረጋገጥ (COC) የተሰኘው መተግባሪያም በተለይም በቴክኒክና ሙያ ለሚመረቁ ተማሪዎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ስለመሆኑ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና አብራርተዋል።

በመተብሪያዎቹ ይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም