በኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግርን እውን ለማድረግ የዳታ ማዕከላትን የማልማት ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግርን እውን ለማድረግ የዳታ ማዕከላትን የማልማት ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 28/2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግርን እውን ለማድረግ የዳታ ማዕከላትን የማልማት ስራ ትኩረት እንደተሰጠው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ገለጹ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዊንጉ አፍሪካና ከአይሲቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር የዳታ ማዕከላት ለፋይናንስ ዘርፉና ለቴክኖሎጂ እድገት መረጋገጥ ያላቸው ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል።
ዶክተር በለጠ ሞላ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በአግባቡ ለማሳካት የተቀናጀ ትግበራ ውስጥ ተገብቷል።
ለዚህም ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ የዳታ ማዕከል ግንባታ ትኩረት እንደተሰጠው ነው የተናገሩት።
በተለይም በቴሌኮምና ፋይናንስ ተቋማት የዳታ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጠው ዊንጉ አፍሪካ የተሰኘው የግል አልሚ በአይሲቲ ፓርክ ዳታ ማዕከል መገንባቱን ገልጸዋል።
ሌሎች ባለሃብቶችም በፓርኩ ውስጥ ስራቸውን ለመጀመር የሚያስችላቸውን ዝግጅት እየጨረሱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዲጅታል ሽግግርን እውን ለማድረግና ሀገራዊ እድገትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የግሉ ዘርፍ የዳታ ማዕከል ግንባታ ላይ በኢንቨስትመንት እንዲሰማራ ጠይቀዋል።
በዊንጉ አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ወርቁ፤ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ገለልተኛና አስተማማኝ የዳታ ማዕከል አገልግሎትን ለፋይናንስ ተቋማት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህም በኢትዮጵያና በቀጣናው ሀገራት የዲጂታል ትስስርን ለማጠናከር መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
የአይሲቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን ስራ አስፈፃሚ ሄኖክ አህመድ በበኩላቸው፤ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአይ ሲቲ ፓርክ ውስጥ የዳታ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረም ጠቁመዋል።