በመልካም ስነምግባር የታነጸና ሀገር ወዳድ ትውልድ ለማፍራት ከመምህራን እና ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ብዙ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በመልካም ስነምግባር የታነጸና ሀገር ወዳድ ትውልድ ለማፍራት ከመምህራን እና ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ብዙ ይጠበቃል

ጂንካ፤ጥቅምት 28/2016(ኢዜአ)፦በመልካም ስነምግባር የታነጸና ሀገሩን የሚወድ ትውልድ ለመፍጠር መምህራንና የትምህርት ማህበረሰቡ የሚጠበቅባቸውን ጥረት እንዲያጠናክሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አስገዘነቡ ።
በክልሉ የትምህርት ሥራዎች ላይ ለመምከር በጂንካ ከተማ በተዘጋጀው ጉባኤ በቀጣይ ሶስት አመታት በሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚተገበሩና የትምህርት ጥራቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራሉ ተብሎ የታመነባቸው ስድስት ነጥቦች ይፋ ተደርገዋል ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከ2016 እስከ 2018 ባሉት ቀጣይ ሶስት አመታት በሁሉም መስክ በተለይም በትምህርቱ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ ልዩ ግብ ተቀምጦ ርብርብ ይደረግባቸዋል።
የውስጥ አቅምን በተደራጀና በአግባቡ በመምራትና በመጠቀም የትምህርት ቤቶች ደረጃና ጥራት ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ስራ ለማጠናከር ግብ መቀመጡን አንስተዋል።
በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት በተቀመጠው ደረጃ መሰረት ንድፍን ከተግባር አዋህዶ የሰለጠነ ና ተወዳዳሪነትን ዓላማው ያደረገ ትውልድ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በትምህርት ጥራት ስብራት መንስኤና መፍትሄ ዙሪያ በተደረገው ምክክር በቀጣይ ሶስት አመታት በሁሉም የክልሉ ትምህርት ቤቶች በልዩ ትኩረት ይተገበራሉ የተባሉና ''የጂንካ ስምምነት'' የሚል መጠሪያ የተሰጠው የአቋም መግለጫ ወጥቷል።
ስምምነቱም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ተቋማዊ አሰራር መዘርጋትና መፈፀም፣ የትምህርት መሰረተ-ልማትን ማጠናከር፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሁሉም ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ማድረግን ያካተተ ነው።
እንዲሁም የመማሪያ መፃህፍትን በራስ አቅም ሟሟላት፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል እና ተከታታይነት ያለው የመምህራን አቅም ግንባታ ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ነጥቦችም በ''ጂንካ ስምምነት'' ውስጥ የተካተቱ ናቸው።
አስተያየታቸውን የሰጡት የኮንሶ ዞን የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኩሴ ጭሎ በትምርት ቤቶች ደረጃና ጥራት መሻሻል ዙሪያ በጥልቀት በመምከር የጋራ አቋም መያዛቸውን ተናግረዋል።
የጋሞ ዞን የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም አምሳሉ በበኩላቸው በጉባኤው ላይ ጠለቅ ያለ ውይይት በማድረግ ስምምነት የተደረሰባቸው ነጥቦች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ወሳኝ ነጥቦች መሆናቸውን አንስተዋል።
የአሌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኅላፊ አቶ አስጨናቂ አሻግሬ በበኩላቸው የትምህርት መሰረተ ልማቶች ጉድለቶችን ለማሟላት የአካባቢውን ማህበረሰብ ባሳተፈ መልኩ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።