ቀጥታ፡

የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች ለዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ስኬት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዳማ፤ ጥቅምት 28/2016 (ኢዜአ) ፦በየደረጃው ያሉ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች ለዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ስኬት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጠየቀ።

አደረጃጀቶቹ በበዓሉ ዝግጅትና መርሐ ግብር ላይ በቂ ግንዛቤ አግኝተው ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና በአዳማ ተካሂዷል።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግስታት ግንኙነት፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና የህገ መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሀፊ ወይዘሮ ባንችይርጋ መለሰ እንደገለፁት፤ የበዓሉ መከበር ኢትዮጵያን ብዝሃነትን በማስተናገድ   ሀገር መገንባት እንደሚቻል ያሳየ ነው።

''ህብረ ብሔራዊነት የኢትዮጵያ መገለጫ ነው'' ያሉት ወይዘሮ ባንችይርጋ፤ ብዝሃነትን ተቀብሎ በአግባቡ ማስተናገድ ብዙ መልካም ጥቅሞች አሉት ብለዋል።

አደረጃጀቶቹ በተለይም ህብረተሰቡን በህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምና በህገ መንግስቱ አስተምህሮ ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ ለበዓሉ ስኬት ሚናቸውን እንዲወጡ ነው የጠየቁት።


 

በዚህም ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናክር እንዲሁም የህዝቦች መቀራረብና ትስስር እንዲጎለብት ማህበረሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ እንዲጨብጥ ማስቻል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

18ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል መጪው ህዳር 29 ቀን 2016ዓ.ም በሱማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ "ብዝሃነትና ዕኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሐሳብ እንደሚከበር ጠቁመዋል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዓለሚቱ ዑመድ በበኩላቸው የበዓሉን አከባበር ውጤታማ ለማድረግ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች በንቃት ይሳተፋሉ ብለዋል።

በተለይም በየደረጃው ያሉ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች በፌዴራላዊ ስርዓቱና በህገ መንግሥቱ አስተምህሮ ላይ ህዝቡን በተገቢው መንገድ ለማስገንዘብ የሚጠበቅባቸውን ይወጣሉ ነው ያሉት።

በምክር ቤቱ የተዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠናም በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የሚገኙ አደረጃጀቶች በዓሉን ስኬታማ ማድረግ እንዲችሉ ያግዛቸዋል ብለዋል።

በአሰልጣኞች ስልጠናው ላይ ከሁሉም ክልሎች የተወከሉ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች እንዲሁም  አመራሮችና አባላት ተሳትፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም