ቀጥታ፡

የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችል እገዛና ድጋፍ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 28/2016 (ኢዜአ) ፦ በተለያዩ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችን በመደገፍ ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩን ጨምሮ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሸገር ከተማ ሰበታ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን የዎዳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጎብኝተዋል።


 

ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎቹ በኢንዱስትሪ ፓርኩ እየተመረቱ ያሉ ምርቶችን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን ተቋሙ በጠየቀው የማስፋፊያ ቦታ ጉዳይም ውይይት አድርገዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በዘርፉ ልማት ለተሰማሩ ባለሀብቶች ድጋፍና እገዛ እየተደረገ ይገኛል።

በተለያዩ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት እና ወደ ውጭ ምርቶችን የመላክ አቅሞችን በማጠናከር የውጪ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ፤ የክልሉ መንግስት ለባለሀብቶች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።


 

የማስፋፊያ ቦታ የመሬት ጥያቄ ያቀረቡ አልሚዎች በየደረጃው ታይቶ ምላሽ የሚያገኙ ይሆናል ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፤ የጉብኝቱ አላማ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችንና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት መሆኑን ገልጸዋል።


 

የዎዳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ምክትል ስራ አስኪያጅ ደረጀ በድሉ፤ አሁን ላይ በ20 ሄክታር ላይ ድርጅቱ እያመረተ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ወደ 100 ሄክታር ለማስፋት ለመንግስት የማስፋፊያ ጥያቄ አቅርበናል ብለዋል።


 

የዋዳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የኤሌክትሪክ ታዎር፣ ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የኤሌክትሪክ ኬብል/ሽቦ እና የቴሌኮም እና ሌሎችንንም ምርቶች እያመረተ መሆኑን ገልጸዋል።

በድርጅቱ ለ400 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ለ10 ሺህ ሰዎች የስራ እድል የሚፈጠር ይሆናል ብለዋል።

 

 

 

 
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም