ቀጥታ፡

የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ እምቅ የቱሪዝም ኃብቶች በስፋት የተዋወቁበት ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 28/2016 (ኢዜአ) ፦ አገር አቀፉ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ የኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ኃብቶች በስፋት የተዋወቁበት የተሳካ መርሃ ግብር መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሳይንስ ሙዚየም በይፋ መከፈቱ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክትም ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪክና ቅርስ፣ የነባር ባህል፣ የውብ መልከዓ ምድር፣ የብርቅዬ እፅዋት፣ አእዋፋትና እንስሳቶች ባለቤት በመሆኗ ለቱሪዝም እድገት መሰረት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ከዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት በማሻሻል ረገድ አሁንም በርካታ ስራዎች ያስፈልጋሉ ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

እስከ ትናንት በቆየው አውደ ርእይም በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪዝም ኃብቶች፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የኪነ ጥበብ ኃብቶችና ልዩ ልዩ ባህሎች ለእይታ ቀርበው የማጠቃለያ ፕሮግራም ተካሂዷል።

በአውደ ርእዩ የማጠናቀቂያ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ ቆይታው የተሳካ ውጤት የተገኘበት ነው ብለዋል።

በአውደ ርዕይው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሃብቶች በስፋት የተዋወቁበትና በነበሩት የውይይት መድረኮች ለዘርፉ እድገት ጠቃሚ ግብአት የተገኘበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ ተሞክሮ በመነሳትም በቀጣይ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የዘርፉ ተዋንያኖች የሚሳተፉበት መርኃ-ግብር የማዘጋጀት እቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።

በአውደ ርዕዩን 154 ሺህ 799 የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች በአካል እንዲሁም ከ9 ሚሊየን በላይ ሰዎች በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች መጎብኘታቸውን ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አሸናፊ ሙሉጌታ፤ አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን ሰፊ የቱሪዝም ሃብቶች በማስተዋወቅ ረገድ የተሳካ ሁነት እንደነበር ገልጸዋል።


 

የአውደ ርእዩ ተሳታፊዎችም ሁነቱ የኢትዮጵያ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በማጠቃለያ መርኃ ግብሩ ለአውደ ርዕዩ መሳካት የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና በማቅረብ እውቅናም ተሰጥቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም