የዓለም የጥራት ቀን ኢትዮጵያውያን አምራቾች የምርት ጥራት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በሚያስችሉ ሁነቶች ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም የጥራት ቀን ኢትዮጵያውያን አምራቾች የምርት ጥራት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በሚያስችሉ ሁነቶች ይከበራል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 28/2016(ኢዜአ)፦ የዓለም የጥራት ቀን ኢትዮጵያውያን አምራቾች የምርት ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ በሚያስችሉ ሁነቶች ከነገ ጀምሮ እንደሚከበር የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በምርቶችና አገልግሎቶች የጥራት ፍተሻ፣ የኢንስፔክሽንና የሰርቲፊኬሽን አገልግሎቶችን በመስጠት ጥራት ያለው ምርት እና አገልግሎት እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የዘንድሮን የዓለም የጥራት ቀን በኢትዮጵያ ለ12ኛ ጊዜ ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 1 ቀን 2016 ዓ.ም “ጥራት፡ ለተሻለ የመወዳደር አቅም” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከብር በመግለጫው ተመላክቷል።
የዓለም የጥራት ቀን 'የምርቶችና አገልግሎቶች ጥራት' በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ኑሮ፣ በድርጅቶች ስኬታማነትና በሀገር ዕድገትና ብልፅግና ላይ የሚጫወተውን የላቀ ሚና ለማስገንዘብ እንደሚከበርም በመግለጫው ተመላክቷል።
እለቱ የሚከበረው የጥራት ግንዛቤን ለማሳደግ፣ ለግለሰቦችና ድርጅቶች ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናና ስኬት እንዲሁም ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ደረጃዎችን ለማዳበር በማለም ነው።
በዚሁ ወቅት የጥራት ማረጋገጫ ያገኙ አምራቾች የሚሳተፉበት የጥራት ኤግዚቢሽንና የጥራት ፍተሻ የሚሰጥባቸው ላብራቶሪዎች የጉብኝት ፕሮግራም መዘጋጀቱ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የምርትና የአገልግሎት ጥራትን በሚመለከት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርቡበት አውደ ጥናት እንደሚካሄድም ተጠቅሷል።
የዘንድሮው የዓለም የጥራት ቀን መሪ ቃል የተወዳዳሪነት አቅምን እውን ለማድረግ ጥራት የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና ለማስገንዘብ በማለም የተቀረጸ መሆኑ ተመላክቷል።
አምራችም ሆነ አገልግሎት ሰጪ ኢንዱስትሪዎች ዓለም በሚመራበት የገበያ ሥርዓት ውስጥ ተጠቃሚ የሚሆኑት በምርትም ሆነ በአገልግሎት ጥራት የተወዳዳሪነት ብቃታቸውን ከፍ ማድረግ ከቻሉ ብቻ ነው።
እለቱ የጥራት ማረጋገጫ በማግኘት ምርታቸውን ለገበያ የሚያቀርቡ አምራች ድርጅቶች ከነገ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ምርታቸውን ያቀርባሉ።
አምራቾች በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲታወቁና ጥራቱ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ምርት ለሸማቹ እንዲያቀርቡ የሚያግዝ ነው ተብሏል።
የዘንድሮው የዓለም የጥራት ቀን ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ የጥራት ማረጋገጫ ያገኙ አምራቾችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በነገው ዕለት በይፋ ይከፈታል።
የመጀመሪያው የዓለም የጥራት ቀን እ.ኤ.አ. በ2008 በለንደን፣ ዩናይትድ ኪንግደም መካሄዱን መረጃዎች ያመላክታሉ።