የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ከ154 ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ጎብኝተውታል - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ከ154 ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ጎብኝተውታል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 27/2016 (ኢዜአ) ፦ አገር አቀፉን የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ከ154 ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች መጎብኘታቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መስከረም 29/ 2016 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው አገር አቀፍ አውደ-ርዕይ የማጠቃለያ መርኃ ግብር ተካሂዷል።
በአውደ ርዕዩ በየክልሎቹ የሚገኙ ባህል፣ እሴቶችና የቱሪዝም ኃብቶች የተዋወቁበት ሲሆን ልዩ ልዩ ሁነቶችና የውይይት መድረኮች ተካሄደዋል።
አውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪዝም ኃብቶችን፣ የማኅበረሰቡን ታሪክና ልዩ ልዩ ባህሎች ለማስተዋወቅ አስተዋጽኦ ማድረጉም ተገልጿል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በአውደ ርዕዩ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሥፍራዎች፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የኪነ ጥበብ ኃብቶችና ሌሎች መሰል የዘርፉ ፀጋዎችና አገልግሎቶች ለእይታ መቅረባቸውን ገልጸዋል።
አውደ ርዕዩን 154 ሺህ 799 የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች በአካል እንዲሁም ከ9 ሚሊየን በላይ ሰዎች በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች መጎብኘታቸውን አመልክተዋል።
በማጠቃለያ መርኃ ግብሩ ለአውደ ርዕዩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።